Search

ካባ እና ከረባት በማስወለቅ ተሳታፊዎችን ያቀራረበው የጣና ፎረም

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 9729

11ኛው የጣና ፎረም ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ እና ባህርዳር ከተሞች "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

ይህ ፎረም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ምሁራን ስለ አህጉሪቱ ጉዳዮች በግልጽ የሚወያዩበትና ለችግሮች መፍትሄ የሚያፈላልጉበት መድረክ ነው።

የመጀመሪያው የጣና ፎረም በባህር ዳር ሲካሄድ፣ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ባህላዊ ካባቸውን አውልቀው በማስቀመጥ ስብሰባውን መክፈታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሜርሲ ፍቃዱ (ዶ/ር) አስታውሰዋል።

ሜርሲ ፍቃዱ (ዶ/ር) ለኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 እንደተናገሩት፣ ያኔ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ፎረሙ "ሁላችንም እኩል ሁነን በአፍሪካ ችግር ዙሪያ ዛፍ ስር ቁጭ ብለን የምንመክርበት ነው" ማለታቸውንም አውስተዋል።

ይህን ተከትሎም ሌሎች መሪዎች ሱፍና ካራባታቸውን አውልቀው በጃኬት ወደ ውይይቱ ተመልሰውም እንደነበር ነው የገለፁት።

የጣና ፎረም ተሳታፊዎች ቀለል ያሉ ልብሶችን እንዲለብሱ የሚመከር ሲሆን፣ ከመድረኩ ጎን ለጎን ችግኝ የመትከል ሥነ ስርዓት እንደሚከናወን እና የስልጣን ወይም የትምህርት ደረጃ ሳይገድብ ሁሉም እኩል የሚነጋገሩበትን ስሜት ለመፍጠር ያለመ መድረክ መሆኑን ሜርሲ ፍቃዱ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የጣና ፎረም ዓላማ የአፍሪካ ሀገራት በደህንነት ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው መርዳት ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በመድረኩ የሚነሱ አንኳር ጉዳዮች ተመርጠው ሪፖርት እንደሚወጣና ለውይይት እንደሚቀርብም አንስተው፤ ይህ አካሄድ አፍሪካ ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ተመካክሮ አፍሪካዊ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳል ይላሉ።

በፎረሙ የጣና ፎረም ቦርድ አባል የሆኑት የቀድሞው የቡርኪናፋሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ላሲና ዜርቦ፤ የቀድሞ የማላዊ ፕሬዝዳንት ጆይስ ቤንዳ፤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሀሙድ አሊ የሱፍን ጨምሮ የቀድሞ እና በሥራ ላይ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ወጣቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

በየተመኙሽ አያሌው