Search

የቻይና-አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም አጋርነትን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው - የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ

ረቡዕ ጥቅምት 19, 2018 46

የቻይና-አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም በቻይና ጓንዶንግ ግዛት ጓንጁ ከተማ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።
የፍትሕ ሚኒስትር ወ/ሮ ሐና አርዓያሥላሴ በፎረሙ ባደረጉት ንግግር፤ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) በአፍሪካ ሀገራት እና በቻይና መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ በኢኮኖሚ እድገት እና ሁሉንም ወገን ያከበረ ፖለቲካዊ አጋርነትን እውን በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ የትብብር ሥርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።
 
ፎረሙ ከምን ጊዜውም በላይ ተለዋዋጭ ሆኖ በመጣው የቴክኖሎጂ ሥነ-ምህዳር እና የባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት ፈተና ላይ በወደቀበት ወቅት መደረጉ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
ፎረሙ በፈተናዎቹ እና በመልካም አጋጣሚዎቹ ላይ ቆም ብለን እንድናስብ እና ሀሳባችንን እንድንለዋወጥ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ዐቃቤ ሕግ ገለልተኛነቱን በማረጋገጥ እውነትን የማፈላለግ እና ፍትሕን የማስፈን ኃላፊነቱን በመወጣት ለተባበሩት መንግስታት ዘላቂ ልማት ግብ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት አመላክተዋል።
በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የድርጊት መርሀ-ግብር (2025-2027) ላይ እንደተመላከተው የአፍሪካ ሀገራት እና ቻይና በሰላም እና መረጋጋት ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ባደረጉት ስምምነት መሰረት ከምንጊዜውም በተጠናከረ የትብብር መንፈስ የተጋረጡትን ፈተናዎች ማለፍ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
 
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ እና ሕግ ጉዳዮች ኮሚሽን ፀሐፊ ቼን ዌንኪንግ በበኩላቸው፤ የሕግ የበላይነት መከበር ለአንድ ሀገር መዘመን የሚኖረውን ገንቢ ሚና በመረዳት ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በቀጣይ በአፍሪካ ሀገራት እና ቻይና የእርስ እርስ የልምድ ልውውጦችን በማድረግ በጋራ አብረው መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ሞዛምቢክ፣ ናጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ በጠቅላይ ዐቃብያነ ሕጎቻቸው እና ልዑካን ቡድኖቻቸው አማካኝነት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።