ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው ሲል የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
መንግሥት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት እንዲቻል የተኪ ምርት ስትራቴጂን በመቅረጽ ወደ ሥራ በመግባቱ ከፍተኛ ውጤቶች ተመዝገበዋል ብሏል አገልግሎቱ በመግለጫው።
ስትራቴጂው የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ የወጪ-ገቢ ምርት እንዲመጣጠን እና ሀገራዊ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ እያደረገ ይገኛልም ነው ያለው።
በተለይ በውስጥ አቅም መቅረብ የሚችሉ ዋና ዋና የገቢ ምርቶች ተለይተው ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ ትኩረት መደረጉ የውጪ ምንዛሬ ከማዳን እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ፋብሪካዎችን ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓል ብሏል።
የተኪ ምርት ስትራቴጂ በሁሉም ዘርፍ በተሟላ መልኩ ገቢራዊ መደረጉ ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ዘርፉ የተሻለ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ባለፉት 3 ወራት ብቻ በተለያዩ ዘርፎች በተመረቱ ተኪ ምርቶች ከ1 ነጥብ 08 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
እንደ አገልግሎቱ መግለጫ፥ ከሀገራችን ነባራዊ የፍጆታ ፍላጎት አንፃር የትኞቹ ምርቶች በቅድሚያ ይተኩ በሚል በምግብ እና መጠጥ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ በኪሚካል እና ኮንስትራክሽን፣ በብረታ ብረት እና በቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር 96 ተወዳዳሪ ተኪ ምርቶች ተለይተው በሀገር ውስጥ ለመተካት የተደረገው ጥረት እንደ ሀገር ፍሬ እያፈራ ይገኛል።
ለአብነትም በ2017/18 የምርት ዘመን የጥጥ ምርት ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ለጥጥ ምርት ተስማሚ በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው 110 ሺህ ሄክታር መሬት በጥሬ ጥጥ 1.9 ሚሊዮን ኩንታል የተገኘ ሲሆን፤ ከዚህም ወደ 66 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ማግኘት ተችሏል።
በዚህም በዘንድሮው የምርት ዘመን ለኢንዱስትሪዎች የሚፈለገውን ያህል የጥጥ ምርት በመጠን እና በጥራት ማቅረብ ተችሏል።
የማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት ችግር እንዳይገጥማቸው በሀገር ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በውጤቱም እሴት የታከለበትን የሀገር ውስጥ ምርት 60 በመቶ ለማድረስ እና የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ትኩረት ተደርጓል ሲል የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
#ebcdotstream #ethiopia #gcs #importsubstitution