Search

ኩታ ገጠም የመኸር ግብርና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል

ሰኞ ጥቅምት 24, 2018 46

የምግብ ዋስትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት መጠናከሩን የሚያሳይ ሥራ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተከናወነ ይገኛል።
በክልሉ ካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴን በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
አርሶ አደሮቹ የመኸር የስንዴ ልማትን በኩታ ገጠም ማከናወናቸው ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በቅንጅት እንዲጠቀሙ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ማሳቸውን በጋራ የመንከባከቡ ሥራ የሕብረተሰብ ትስስርን ለማጠናከር አይነተኛ መንገድ መሆኑን ይገልጻሉ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ መረጃ መሰረት፣ በክልሉ በመኸር እርሻ ከ420 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ በዘር ተሸፍኗል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ፣ በመኸር ግብርናው ከ18.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ የክልሉን የግብርና እምቅ አቅም አያደገ መሆኑን አንስተዋል።
የምርት ዘመኑ ተስተካክሎ በተገኘው የዝናብ ስርጭት፣ በቂ የግብዓት አቅርቦት እና በግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ድጋፍና ክትትል ማሳዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል ይላሉ።
አርሶ አደሮቹ ከማሳቸው በሔክታር እስከ 50 ኩንታል የሚደርስ ምርት ለመሰብሰብ ዝግጅት ማድረጋቸውም ተመላክቷል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፤ በዞኑ ከ123 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ መልማቱን እና ከ2.8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
‎ኢትዮጵያ ከመኸር ሰብል 653 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራች ይገኛል።
 
በሰለሞን ባረና