ኢትዮጵያ ከፈረንሳዩ ኩባንያ 'ኤሊክቲሪሲቲ ደ ፍራንስ' (EDF) ጋር መካከለኛ የኃይል መስርመር ዝርጋታ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርማለች፡፡
በኢትዮጵያ - አውሮፓ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ስምምነት ባካሄዱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ሥምምነቱ በሥልጠና እና ቴክኒክ ላይ አብሮ ለመስራትም የሚያስችል ነው፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር ይህንን አስመልክቶ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለጹት፤ በሥምምነቱ ያረጁ መካከለኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በመቀየር፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የኔትወርክ ጥገናን በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይልን በዘመነ መልኩ ወደ ኢንዱስትሪዎች ለማድረስ ያስችላል፡፡
ይህ ሥምምነት ተግባራዊ ሲደረግም የቴክኒክ አቅምን በማሳደግ፣ የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ የዘመናዊነት ጉዞ ይበልጥ ወደፊት የሚያራምድ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመካከለኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ከ40 ዓመታት በላይ ያገለገሉና ያረጁ በመሆናቸው፣ አስተማማኝ ኃይል ለማስተላለፍ የሚያዳግቱና ለአደጋ የሚያጋልጡ ስለመሆናቸው አቶ አንዋር ተናግረዋል፡፡
በመሐመድ ፊጣሞ