Search

ለቸኮሌት ምርት እጅግ ተፈላጊ የሆነው ካካዎ

ማክሰኞ ጥቅምት 25, 2018 11168

የካካዎ ምርት በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ እጅግ ተፈላጊ እየሆነ በመምጣቱ ሀገራት ዘሩን ከሀገራቸው የአየር ንብረት ጋር በሚዛመድ መልኩ በማሻሻል በማምረት ላይ ይገኛሉ።

በሀገራችን ኢትዮጵያም ካካዎን ለማምረት የምርምርና የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በቅርቡም ይህንን ትኩረት ሰጥቶ ዘሩን በማስፋፋት ላይ የሚገኘው የቴፒ የግብርና ምርምር ማዕከልና ሌሎች የእርሻ ምርምር ማዕከላት አማካኝነት 50 በላይ የካካዎ ችግኞች ተባዝተው ለዘንድሮ ተከላ ዝግጁ ተደርገዋል።

ኢትዮጵያ ለዚህ ተክል አመቺ የሆነ የአየር ንብረት ካሏቸው ሀገራት አንዷ በመሆኗ በቀጣይ ምርቱን አስፋፍቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራበት መሆኑ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው።

ስለ ካካዎ ዛፍ ጥቂት ነጥቦች

አንድ የካካዎ ዛፍ ከአምስተኛው ዓመት በኋላ ሙሉ ምርታማነት ደረጃ ላይ ይደርሳል።

አንዴ ምርት መስጠት ከጀመረ በኋላ ባሉት 30 ዓመታት ድረስም ጥሩ ምርት እየሰጠ የሚቆይ ሲሆን፣ በእድሜ ረገድ ግን የተወሰነ ምርት እየሰጠ እስከ መቶ ዓመታት ድረስ መቆየት የሚችል ተክል ነው።

ይህንን ተክልም ከምርምር ተቋማት ባለፈ በግለሰቦች እርሻ ላይ ማስፋፋት የሚቻልበት ዕድል ስለመኖሩም ማሳያ የሆነ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

የጋና የካካዎ ምርት ተሞክሮ

በዓለማችን ላይ ለሚገኙ የቸኮሌት ፋብሪካዎች ሁሉ ዋና ጥሬ ዕቃ የሆነው የካካዎ ተክል በተለያዩ የደቡብ አሜሪካና የእስያ አገራት በሰፊው የሚበቅል ሲሆን፣ በአፍሪካ ደግሞ ኮትዲቯር እና ጋና ምርቱን በስፋት ለውጭ ገበያ በመላክ ይታወቃሉ።

ዛሬ ላይ በዓለም ላይ ለሚመረቱ የቸኮሌት ምርቶች ዋና ጥሬ ዕቃ የሆነውን የካካዎ ምርት ከሚያቀርቡ አገራት መካከል ጋና ዋነኛዋ ነች።

ይህች አፍሪካዊት አገር በስፋት ከምታመርተው የካካዎ ምርት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ የምታገኝ ሲሆን፣ ባለፈው 2021 ከላከችው ምርት 2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት ችላለች።

ካካዎ ለጋና የኢኮኖሚ አቅምን ከማገዝ ባለፈ እስከ 800 ሺህ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለው ነው።

አፍሪካዊቷ ጋና በዓለም የካካዎ ምርትን በመላክ ሁለተኛዋ አገር እንድትሆን ያስቻለ ሠፊ ሥራ በማከናወን ረገድም ቴቴህ ኳርሺ የሚለው ስም በሰፊው ይነሳል።

ይህ ሰው በስደት በሄደበት ጊኒ በሰፊው ሲለማ ያየውን የካካዎ ተክል በሀገሩ ለመትከል በማሰብ ፍሬውን ይዞ በመምጣት በየዓመቱ ለምታገኘው ቢሊዮን ዶላሮች መሠረት የሆነ የሀገር ባለውለታ መሆን የቻለ ሰው ነው።

ዛሬ ጋና በሚል ስም በምትታወቀው በያኔዋ ጎልድ ኮስት የተወለደው ቴቴህ ኳርሺ በሙያው የብረታ ብረት ሠራተኛ ነበር። በዚህ ሙያውም ለመስራት 1870ዎቹ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ተጓዘ።

ቴቴህ የብረታ ብረት ሥራውን ለመስራት በሄደበት በዚህ በኢኳቶሪያል ጊኒ ቆይታው የተመለከተው የካካዎ ተክል ትኩረቱን ሳበው። ይህን ፍሬ ይዞ ወደ ሀገሩ ቢመለስ የሀገሩን ዕጣ ፈንታ የመለወጥ አቅም እንዳለው በማመኑ 1879 ወደ ሀገሩ ሲመለስ በብረታ ብረት ሳጥኑ ውስጥ በርካታ የካካዎ ፍሬዎች ደብቆ ካስቀመጠ በኋላ ወደ ጋና ይዞ መጣ።

ይህንን ሀሳብ በውስጡ የያዘው ቴቴህ ዘሩን ብቻ ይዞ መምጣት ሳይሆን፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ ቆይታው በካካዎ እርሻ ቦታ ለተወሰነ ጊዜ በመስራት የካካዎ ተክል እንዴት መዝራት እና ማብቀል እንደሚቻል ተምሮ ነበርና ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ በአክዋፒም ማምፖንግ የእርሻ ቦታው ላይ ዛሬ ጋናን የዓለማችን ቀዳሚ ያደረጓትን የመጀመሪያዎቹን የካካዎ ችግኞች አዘጋጅቶ ተከለ።

ቴቴህ ኳርሺ የካካዎን ተክል በጋና ማብቀል ከመጀመሩ በፊት በሀገሪቱ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሚሲዮናውያን የጋና የአየር ሁኔታ ለዚህ ተክል ምቹ መሆኑን ተረድተው ካካዎ ለመትከል ሞክረው ነበር። ሆኖም ትክክለኛውን የአበቃቀል ዘዴ ባለማወቃቸው በሚሲዮናውያኑ ተሞክሮ የነበረው ካካዎን በጋና ምድር የማብቀል ሙከራ በቴቴህ ኳርሺ ተሳካ።

ዘሩ መብቀል መጀመሩን ያስተዋለው ቴቴህ ይህንን ውድ ተክል ለራሱ ብቻ ይዞ አልተቀመጠም። ህልሙ ሀገሩ በዚህ ተክል ተጠቃሚ እንድትሆን ነውና ያመጣውን ፍሬ በተገቢው መንገድ ችግኝ እያዘጋጀ በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎችና ለዘመዶቹ በነፃ እያደለ የካካዎ ዛፍ በፍጥነት እንዲስፋፋ ማድረግ ጀመረ።

በዚህ መልኩ ካካዎን ከሀገሩ ጋና ጋር ያስተዋወቀው ቴቴህ ዛፎቹን እየተንከባከበ በአምስተኛው ዓመት ለጋና ምድር እንግዳ የነበሩት የካካዎ ዛፎች የመጀመሪያ ምርታቸውን መስጠት ጀመሩ።

በኋላም የካካዎ ምርቱ በአርሶ አደሮች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ከዓመት ዓመት እየተስፋፋ ጋናን ከዓለማችን ግንባር ቀደም አምራች ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ተቻለ።

ለሀገሩ ትልቁን የኢኮኖሚ መሠረት ጥሎ ያለፈው ቴቴህ ኳርሺ ዛሬ ላይ በጋና አደባባዮች፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታል በስሙ ተሰይሞለታል።

እንዲሁም የመጀመሪያዎቹን የካካዎ ፍሬዎች የተከለበት በአክዋፒም ማምፖንግ ያለው የእርሻ ቦታ እንደ ሙዚየም የሚጎበኝ የቴቴህ መታሰቢያ ቦታ መሆን ችሏል።

የቴቴህ ኳርሺ ታሪክ መነሳሳትና ራዕይ ካለ የበርካታ ሚሊዮኖችን ሕይወት የሚቀይር ታላቅ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችል የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ ታሪክም ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገች ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረግኩ ብሎ መጠየቅ እና ተግቶ መሥራት ለውጤት እንደሚያበቃ ነው።

ኢትዮጵያም በምርምር ተቋማቷ በኩል የጀመረችውን ካካዎን የማላመድ እና የማስፋፋት ሥራ ብዙዎች ዘንድ ደርሶ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያስገኝ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ