አራዳ፣ ጃንተከል እና ቆብ አስጥል ዳግም ካልተወለዱ በጎንደር ከተማ ታሪክ ተደግሟል ማለት እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ላለፉት 30 ዓመታት የጎንደር ከተማን እንደሚያውቁ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፋሲል ታድሷል የሚለው አገላለጽ እንደማይመጥነው እና ዳግም መወለዱን ገልጸዋል።
ለጎንደር መመሥረት መነሻው የፋሲል ቤተመንግሥት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ቤተ መንግሥቱ የፈጠረው ከባቢ ዳግም ካልተወለደ የጎንደር ዳግም መወለድ ሙሉ እንደማይሆን ተናግረዋል።
"ጎንደር እንደ ፋሲል ዳግም ራሷን ወልዳ ማየት የሁላችንም መሻት፣ ምኞት እና ሥራ መሆን አለበት" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
"ከአዘዞ ጀምሮ እስከ ፒያሳ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ጎንደር ዳግም ለመወለድ እያማጠች እንደሆነ ያሳያል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምጡ አሁን ባለበት ከቀረ ስለሚጨነግፍ አዋላጅ ባለሙያ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
አክለውም፣ "ደግፈን፣ አግዘን እንዲወለድ ካደረግነው ግን በፋሲል ምድረ ግቢ የሚታየው ውበት በመላዋ የጎንደር ከተማ ሊታይ ይችላል" ብለዋል።
ጎንደር በዘመናት መካከል አሁን ምርጥ ከንቲባ ማግኘቷን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለጎንደር ዳግም መወለድ ይህን ዕድል መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በሌሎች ጉዳዮች ልዩነት ቢኖር እንኳን ጎንደርን በማልማት ጉዳይ ላይ ግን ልዩነት ሊኖር እንደማይገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።
በቅርቡ ከውጭ የመጡ እንግዶች ከጎንደር እስከ ባሕር ዳር ጉብኝት ማድረጋቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ጠንክራ ብትሠራ የትም ቦታ የማይገኙ ፀጋዎች እንዳሏት እንግዶቹ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBCdotstream #AbiyAhmedAli #Gondar #asil