Search

ዛሬ ለመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ታሪካዊ ቀን ነው - የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

ዓርብ ጥቅምት 28, 2018 37

የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት ዛሬ በፕሮጀክቱ ግንባታ ሒደት ታሪካዊ ቀን ሆኗል ሲሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለፁ።
ከዚህ ቀደም ሕዝቡ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያነሳ እንደነበርም ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እንደአደረገ ጠቁመው፤ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ልዩ ትኩረት እና በተደረጉት የአሰራር ለውጦች አማካኝነት የፕሮጀክቱ ችግሮች ከስር መሰረታቸው መፈታታቸውን አስረድተዋል።
ቆሞ የነበረው የስትራክቸር ሥራም እንደተጠናቀቀ እና የዋናው ግድብ የአፈር ሙሌት ሥራውም በስፋት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በቅርቡም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለምርቃት እንደሚበቃ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት መገምገሙን አመላክተው፤ ግድቡ በሚጠናቀቅበት ወቅት የአካባቢውን የግብርና ምርታማነት እንደሚያሳድግ በማኀበራዊ የትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል።
የፕሮጀክቱ ቁልፍ የሆነው የወንዝ ቅልበሳ ሥራ በተሳካ መልኩ መጠናቀቁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
 
በሜሮን ንብረት