የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዳይረፍድብን ተባብረን እንሥራ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር በመሆን እድሳት የተደረገለትን የፋሲል ግቢ ዛሬ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ እንዳይረፍድብን ተባብረን እንሥራ፤ ከዘገየን ልክ አይመጣም ሲሉ ገልጸዋል።
የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው ጎንደር በጎብኚዎች እጅግ የምትደነቅ መሆኗን ጠቁመው፤ ከጎንደር-ጎርጎራ ያለውን መንገድ እንዲሁም መልማት ያለባቸውን የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በይበልጥ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።
ልዩነቶች ቢኖሩም ለሀገር ዕድገት እና ለልጆቻችን ያማረ ነገን በጋራ ለመገንባት፣ በአንድነት ማልማት አለብን ብለዋል።
አክለውም ጎንደር ዳግም ተወልዳና አሸብርቃ ጥንታዊነቷን፣ ታሪኳን ሳትለቅ ለዓለም አስደናቂ ከተማ እስክትሆን ድረስ በትጋት፣ ታላቅ ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጉልበት ይሸሻል፣ ጊዜ ይሸሻል፣ ሥልጣን ይሸሻል፣ ሁሉም አላፊ ነው፤ የማያልፈው ታላቅ ሥራ ስለሆነ ታላቅ ሥራ በጋራ እንድንሠራ አደራ እላለሁ ብለዋል።
በሔለን ተስፋዬ