በወርቅ ላይ ቆሞ በአፈር መጣላት፤ በነዳጅ ላይ ሆኖ በውኃ እንደመጨቃጨቅ ያለ አለመታደል ከወዴት ይገኛል ብሎ የሚጠይቅ ጥቂት ጠቢብ በየሀገራቱ አይጠፋም።
አንዳንድ ሀገራት ሀገር መሆን የቻሉት በዜጎቻቸው ነው። አንዳንዶች ደግሞ በተፈጥሯቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉንም አሟልቶ የያዘ ሀገር እንዴት ከእድገት ማማ ውስጥ ስሙ የለም ብሎ ለሚጠይቅ ጎልቶ የሚታየው ምስጢራዊ መልስ ነው።
ተፈጥሮ በድሏቸው በዜጎቻቸው ጥረት ከከፍታ ማማ ለመውጣት ያልተቸገሩ ሀገራት የሰው ልጅ የማሰብ ከፍታ እና የማድረግ ችሎታን የሚያሳዩ ቋሚ ህያው ምስክሮች ናቸው።
የኢትዮጵያን ግማሽ ያህል የቆዳ ስፋት ያላት ዩክሬን ከዓለም ትልቅ ስንዴ አምራቾች መካከል የሆነችበት ዘዴ ትልቅ ምሳሌ ነው።

አምስት ወራት ገደማ በበረዶ ተሸፍና እንኳን ምርት ለማምረት ለመኖር በሚያዳግት የአየር ጸባይ ውስጥ የምታልፈው ዩክሬን በቀሪ ወራት የምትሰራው ሥራ ግን ስሟን በዓለም ከፍተኛ አምራቾች ውስጥ ማስገባት ችላለች።
ይህ ሁሉ ሆኖ ከሀገሯ አልፋ ለዓለም የግብርና ምርቶች አቅራቢ እስከመሆን ደርሳለች።
ታዲያ ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በቂ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውኃ፣ ምቹ የአየር ንብረት ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጋር የታደለችው ኢትዮጵያ ለዘመናት ቢያንስ ስንዴን ለራሷ ፍላጎት እንኳን ማምረት እንዴት ተሳናት?
በእርግጥ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በልኳ ማምረት ተስኗት የቆየውን የስንዴ ምርት ታሪክ እየቀለበሰች እንደውም ወደውጭ መላክ ጀምራለች።
እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ ዩክሬን በግማሽ ዓመት ብቻ ለዛውም ከኢትዮጵያ ባነሰ የመሬት ስፋት ላይ እንዴት ከእኛ የተሻለ አምራች ሆነች? እንዲህ ያለው የተገላቢጦሽ ታሪክስ የት ጋር ነው ያለፈን? አሁንስ የት ላይ ነን? የሚለው ነው።
ይህ ጉዳይ ሁለት የዳቦ ቅርጫት የመሆን አቅም ያላቸው ሀገራት እንዴት የተለያየ ቦታ ተቀመጡ የሚለውን ብቻ ሳይሆን፤ ቴክኖሎጂ፣ ፖሊሲ እና መሠረተ ልማት የግብርና አቅምን እንዴት ከፍ እና ዝቅ ሊያደርጉ እንደሚችሉም የሚያሳይ ጭምር ነው።
የራሷን መንገድ ያገኘችው ዩክሬን እንዴት መንገዱን አገኘች የሚለውን ማየት ጠቃሚ ነው።
ምንም እንኳን ዩክሬን ለም የሚባለውን የዓለማችን አፈርን የታደለች ብትሆንም፤ በግብርናው ዘርፍ ጨዋታ ቀያሪ የሆነውን ውሳኔ ወስዳ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበረውን ሥርዓት ወደ ትላልቅ እና የግል ኢንተርፕራይዞች እንዲሸጋገር አድርጋለች።
የዩክሬን ግብርና ሰፋፊ ክላስተር ያላቸው እርሻዎች፣ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ፣ በጂፒኤስ ጭምር የሚመሩ ትራክተሮች እና የላቀ የመስኖ እና የማዳበሪያ አጠቃቀም ሥርዓቶችን ያጣምራል።
ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ እንዲሁም ተባዮችን እና በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነቱንም ከፍ አድርገዋል።
ዘመናዊ የባቡር እና የወደብ ሥርዓትን ጨምሮ ጠንካራ መሠረተ ልማቶች ያላት ዩክሬን እህልን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያዎች በብቃት ለማጓጓዝ ስላስቻላት በስንዴ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን አድርጓታል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ደግሞ በዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነው የግብርና ዘርፍ ረጅም ዓመታትን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሂደት ውስጥ የነበረችው ኢትዮጵያስ የግብርናው መልክ እንዴት ያለ ነው?
“ዓለም አምስተኛው አብዮት ላይ ቢደርስም ግብርናችን እንኳንስ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተሠናስሎና ተቀናጅቶ ውጤት ሊያመጣ ቀርቶ፣ አሁንም ራሱን ችሎ መቆም ተቸግሯል” (የመደመር መንግሥት መጽሐፍ) የኢትዮጵያን ግብርና በግልጽ ያስቀመጠበት አንቀጽ ነው። እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ግብርና በተፈጥሮ ሃብት እና የሰው ኃይል ብቻ እንኳን ብንመዝነው ብዙ ነገሩ ቁጭትን ይቀሰቅሳል።
“ገና ከባህላዊ አሠራሮች ያልተላቀቀ እና ውጤቱም ከሚጠበቀው በእጅጉ አናሳ ነው። እርሻችን ከከብቶች ትከሻና ከሞፈር ቀንበር ላይ አልተላቀቀም፡፡ እጅግ ሲበዛም በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው። የበለጸገው ዓለም ከብዙ ዓመታት በፊት የተወውን የአመራረት ዘዬ የሚከተል ነው።” የሚለው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የግብርናውን ዘርፍ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረ እና የተፈጥሮ ጥገኛ መሆኑንም ይጠቁማል።
ታዲያ በቁጭት ብቻ የሚባክን ሃሳብ ሳይሆን በተግባር የሚታይ እመርታ ለማምጣት ባለፉት 7 ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች እውነትም ኢትዮጵያ ምነው እስከአሁን ትንሽ ሞክራው ቢሆን የሚያስብል የስኬት ቁጭት የተፈጠረበት ሥራ መመልከት ተችሏል።
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ ያልሰራችበትን የግብርና ዘርፍ እያዘመንን፤ ዓለም ከደረሰበት 5ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን እኩል እንዴት እንራመድ የሚለውን እሳቤ በስፋት ያነሳል።
ይህ እሳቤ ኢትዮጵያ ከእሷ በብዙ የተፈጥሮ ምክንያቶች ካነሱ ሀገራት በታች አምራች ሆና እንዳትቀር፤ እርሻዋ ከበሬ ትከሻ እንዲላቀቅ ብሎም ተገቢውን ምርት አምርታ እራሷን ብሎም ዓለምን እንድትጠቅም ልትከተለው የሚገባውን መንገድም የሚያመላክት እና መስመሩንም በተግባር አስጀምሮ እያሳየም የሚገኝ ነው።
ችግር ውስጥ የገባውን የግብርና ሥራ ለትውልድ በሚተላለፍ መልኩ ለማከም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ብዙ ስኬቶች ተመዝግበውበታል። በበጋ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በመስኖ ልማትና በሌሎች የግብርና ዘርፎች ኢትዮጵያ ቀጣይነት ባለው መልኩ የልማት አቅጣጫዋን ለይታ እየሰራችበት መሆኑን ማንም የሚያየው ሆኗል።
እንዲህ ያለው ዘላቂ ሥራ የምግብ ዋስትናን፣ ሥርዓተ ምግብን፣ የምግብ ሉዐላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን በዘላቂነት ለመገንባት መሰረት የተጣለበት ሆኗል።
በሰለሞን ከበደ