Search

የደብረ ብርሃን ጉብኝቴ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር የማድረጊያውን ጭራ መያዛችንን አሳይቶኛል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ማክሰኞ ኅዳር 02, 2018 115

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢንዱስትሪ የስበት ማዕከል” በሆነችው ደብረ ብርሃን ዛሬ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ብራውን ፉድስ የበቆሎ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

በተለይም ዛሬ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ብራውን ፉድስ የበቆሎ ማቀነባበሪያ ፋብሪካየኢንዱስትሪ ጉዟችንን መዋቅራዊ ሽግግር ከሚያሳዩት አንዱ ነው” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሚጨበጥ ብርሃን - በደብረ ብርሃን” በሚል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት።

ፋብሪካው በበቆሎ አምራች ገበሬዎችና በኢንዱስትሪው መካከል ትሥሥርን የሚፈጥር፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የሚተካ እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የበቆሎ ምርቱ በቫይታሚን እና ማዕድናት በልጽጎ፣ የተመጣጠነ ምግብን ለማግኘት በሚያስችል ሁኔታ የሚዘጋጅ ነው፤ ይህም መሰል ምርት ከሚያመርቱ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን አንዷ ያደርጋታል ነው ያሉት።

የደብረ ብርሃን ጉብኝቴ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር የማድረጊያውን ጭራ መያዛችንን አሳይቶኛል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን እጅግ በብዛት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎቻችን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ጉዟችን የሚሳካባቸው መሣሪያዎቻችን ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።