Search

የጣናነሽ ፪ ጀልባ ሥራ መጀመር የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃው ነው - አስጎብኚዎች

ረቡዕ ኅዳር 03, 2018 114

የጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ሥራ መጀመር በጣና ሐይቅ ሲሰጥ የቆየውን የትራንስፖርት አገልግሎት ይበልጥ በማዘመን የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃ መምጣቱን በባሕር ዳር ከተማ የሚሰሩ አስጎብኝዎች ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባን ሥራ በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።
የጀልበዋን ሥራ መጀመር በማስመልከት የባሕር ዳር ከተማ አስጎብኚዎች እንዳሉት፤ የጀልባዋ ወደ ሥራ መግባት በጣና ሐይቅ ላይ የነበረውን የትራንስፖርት አገልግሎት በማዘመን ዘርፉን እያነቃቃው መጥቷል።
ከአስጎብኚዎቹ መካከል አቶ አበበ ያረጋል፤ የጀልባዋን ሥራ መጀመር በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማራው ማህብረሰብ በጉጉት ሲጠብቀው እንደቆየ ተናግረዋል።
ለቱሪስቶች በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ ታሪካዊና ባሕላዊ የመስህብ ሃብቶችን ለመጎብኘት ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱንም ነው የገለጹት።
አክለውም የጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ከነበሩ ጀልባዎች ይልቅ ፈጣን፣ ዘመናዊና ምቾት ያላት በመሆኗ በርካታ ጎብኚዎች ጀልባዋን ለመጠቀም ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሌላው በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማሩት አቶ አበባው ሲሳይ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ጎብኚዎች በአንድ ጊዜ ሲመጡ ለማስተናገድ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
የነበሩ ጀልባዎች አነስተኛና ውስን ሰው ብቻ እንደሚይዙ ጠቁመው፤ ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ብዛት ያለው ሰው የመያዝ አቅም ስላላት ችግሩ መፈታቱን ተናግረዋል።
ጀልባዋ ለጉዞ የሚያስፈልጉ ግብአቶች የተሟላላት በመሆኑም በጎብኝዎች ተመራጭ እንድትሆን እንዳስቻላት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አቶ ኤፍሬም አብርሀም የተባሉ ሌላው አስጎብኚ፤ ሐይቁ የታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መስህብ ሃብት መገኛ በመሆኑ ይሄን ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል የጀልባዋ ሥራ መጀመር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።