Search

በአማራ ክልል እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል፡- የክልሉ ግብርና ቢሮ

ረቡዕ ኅዳር 03, 2018 141

በአማራ ክልል ከመኸር ወቅት እርሻ እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለኢቲቪ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በመኸር ወቅት እርሻ ከ5.4 ሚልዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 5 ነጥብ 5 ማልዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል።
በክልሉ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ እየተሰበሰቡ ከሚገኙ ሰብሎች ውስጥም ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ማሾ፣ ጥጥ፣ ቦለቄ፣ ገብስ እና የመሳሰሉት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በአርሶ አደሮች ማሳ ሰብሎች በሚሰበሰቡበት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት ለመቀነስና ሰብሎችን በወቅቱ በመሠብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከልም፣ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች የተጠናከሩ ድጋፎችን እያደረጉ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሮች በሰብል ስብሰባ ወቅት የምርት ብክነት እንዳይከሰት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እንደ "ደቦ" በመሳሰሉ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመጠቀም በወቅቱ መሠብሠብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ ሰብልን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የመሰብሰቡ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መመጣቱንም የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ዓመትም የተለያዩ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽኖችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።
በክልሉ በመኸር ወቅት የምርት ዘመኑ ከ187 ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
 
በሳሙኤል ወርቅአየሁ