Search

መፍጠር፣ መፍጠን እና በጥራት መሥራት የሁልጊዜም የሥራ መመሪያችን ሊሆን ይገባል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ረቡዕ ኅዳር 03, 2018 122

መፍጠር፣ መፍጠን እና በጥራት መሥራት የሁልጊዜም የሥራ መመሪያችን ሊሆን ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ በነበራቸው ቆይታ፣ የመኪና መገጣጠሚያ እንዲሁም የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻዎችን መመልከታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
በቆይታቸው የተመለከቷቸው ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓትን በመጠቀምና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን እያዳኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከብየዳ ጀምሮ ትላልቅ የኤሌትሪክ አውቶቡሶችን እየገጣጠመ የሚገኘው የፊቤላ ኢንዱስትሪያል መኪና መገጠሚያ፣ በቀን 12 መኪና ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም መገጣጠሚያው በቅርቡ ያስጀመረው አዲስ የቀለም መቀቢያ በርካታ ቀናትን ይወስዱ የነበሩ ሥራዎችን በሰዓታት ለማከናወን እንዳስቻለው ነው የገለጹት፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በአንድ ቀን 450 ሺህ ጠርሙስ የሚያመርተው ዴዴ ቦትል የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻ ደግሞ 86 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ ተጠቅሞ ለበርካታ የመጠጥ እና የመድሃኒት ፋብሪካዎች ጥቅም የሚሰጡ ጠርሙሶች ያመርታል፡፡
በኢንዱስትሪዎቹ የተመለከትናቸው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴዎች በየዘርፉ በጥራትና በፍጥነት በመትጋት የምናልመውን እድገት በአጠረ ጊዜ እንደምናሳካ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡