መንግሥት በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎች እንዲታወቁ፣ እንዲለዩ እና እንዲገለጡ የሰጠው ትኩረት የብልፅግና አቅሞች እንዲደመሩ አስችሏል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
እንደ ሀገር በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎች ታውቀው እና ተለይተው የህዝባችን የኢኮኖሚ መሠረቶች እንዲሆኑ ለማስቻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ተደማሪ አቅምን መፍጠር ችለዋል ብሏል አገልግሎቱ በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ባጋራው መረጃ።
መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም አቅም በመገንዘብ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ክልሎች በየአካባቢያቸው የሚገኙ ፀጋዎችን አልምተው ነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ መልካም ዕድል እየፈጠረ ይገኛል ብሏል።
በተለይ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንዲጠበቁ እና እንዲለሙ በማድረግ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት እንደ ሀገር እመርታ የታየበት መሆኑንም ገልጿል።

በዚህ ረገድ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምስራቅ ጉራጌ ዞን ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ ቅርሶች እና ምድረ ከብድ አቡነ ገብረ-መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም የሚጠቀሱ ናቸው ብሏል።
ጢያ ትክል ድንጋይ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ተብሎ በ1972 ዓ.ም በዩኔስኮ የተመዘገበ ቢሆንም ለዘመናት ትኩረት ተነፍጎት የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች ሳይሟሉለት መቆየቱን አንስቷል።
የኢትዮጵያን ጸጋዎች ሁሉ አሟጦ መጠቀም በሚል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመነጨው ሀሳብ መሠረት መካነ ቅርሱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ተደማሪ አቅም እንዲሆን በሚያስችል መልኩ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እየተሟሉለት ይገኛሉ።
በአካባቢው ያለው የቱሪስት እና የተመራማሪዎች ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው "ጢያ ፕሮጀክት" ሁለት ከተሞችን የሚያገናኝ፣ ባለሀብትን በማስተባበር የሚሠራ እና ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለት ነው።
የጢያ ትክል ድንጋይ ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጥር የቻለ ሲሆን፤ እንደ ሀገር የአከባቢው ፀጋ የሚገለጥበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።