በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ቦታዎች የሀምበርቾ ተራራ 777 ደረጃ አንዱ ነው።
ይህ ስፍራ አሁን ላይ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ሆኗል።
ከከምባታ ሕዝብ ታሪክ ጋር የተቆራኘው ሀምበርቾ ተራራ ከአዲስ አበባ በ260 ኪሎ ሜትር፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ዱራሜ ደግሞ በ8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ እና 777 የመወጣጫ ደረጃ የተሰራለት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ስፍራውን በጎበኙበት ወቅት ተጨማሪ ደረጃዎች እንዲገነቡ ባቀረቡት ሀሳብ መሠረት ዳግም 777 በሚል ተጨማሪ 777 ደረጃዎች ተጨምረውለት በአጠቃላይ 1554 ደረጃዎች በተራራው ላይ ተገንብተዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ የሀምበርቾ ተራራ 777 ደረጃን ከክልሉ የሥራ ሀላፊዎች ጋር ጎብኝተዋል።
ሚኒስቴር ዴኤታው በጉብኝታቸው ወቅት ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያን ከሌሎች የዓለም ሀገራት ለየት የሚያደርጋት ሁሉንም ዓይነት የቱሪዝም አማራጮችን በውስጧ መያዟ ነው።
የሀምበርቾ ተራራ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኑ በፊት የአካባቢው ነዋሪዎች ለመውጣት እና ለመውረድ የሚቸገሩበት ስፍራ እንደነበር ጠቅሰው፤ እይታን መቀየር ከተቻለ ተግዳሮትን ወደ ሀብት መቀየር እንደማያዳግት የሀምበርቾ ተራራ 777 ደረጃ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ተራራ ተግዳሮትን ወደ ፀጋ ለመቀየር ብዙ ጥረት በማድረግ እና ብዙ ላብ በማፍሰስ ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያየንበትም ነው ብለዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነው አመርቂ ውጤቶች እየታዩ ነው የሚሉት አቶ ተስፋሁን፤ ከመዳረሻ አንፃር ግን ተጨማሪ ሥራዎች ይቀሩናል ሲሉ ተናግረዋል።
ያሉንን የተፈፅሮ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎችን መለየት፣ መንከባከብ፣ መጠበቅ እና ማስተዋወቅ ላይ በሰፊው ከተሠራ የቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ እያደገ ይሄዳልም ብለዋል።
የውጪ ቱሪስቶች ፍሰት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅዖው ከፍተኛ ቢሆንም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከኢኮኖሚ በላይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና የጋራ ትርክትን ለማፅናት የላቀ አስተዋፅዖ እንዳለውም አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየለሙ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መልማተ ብቻውን ጥቅም ስለማይኖረው ሁሉም ሚዲያዎች እነዚህን መዳረሻዎች በሚገባ በማስተዋወቅ እንዲታዩ ከማድረግ አንፃር ሚናቸውን በሚገባ መወጣት ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በሃይማኖት ከበደ