በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ሥራዎችን በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
በክልሉ በተካሄደው የአርሶ አደሮች ቀን በዓል ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል ምርትን ለማስፋት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ከተያዙ ዕቅዶች መካከል ግብርና እና የገጠር ኮሪደር ልማት እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ በትኩረት እየተሠራባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበክር ኸሊፋ፥ በምርት ዘመኑ በክልሉ 56 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
በክልሉ አርሶ አደሮች የተለያዩ ሰብሎችን በኩታ ገጠም የማልማት ልምድ እያዳበሩ መሆኑን አንስተው፣ በዓሉ አርሶ አደሮች የልምድ ልውውጥ በማድረግ ምርትን ወደ ኢኮኖሚ እንዲያሸጋግሩ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የባምባሲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አብዱልዋሂድ አዙቤር በበኩላቸው፤ ወረዳው በሠራው አመርቂ የግብርና ልማት ሥራ ክልላዊ የአርሶ አደሮች በዓሉን እንዲያዘጋጅ መመረጡ የተለየ የሥራ ተነሳሽነት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በርዕሰ መስተዳደሩ የተመራው ልዑክ በወረዳው አያንቱ ቀበሌ የለማ 29 ሺህ 500 ሄክታር የበቆሎ ዘር ብዜት ክላስተር፣ በ50 ሄክታር ላይ የለማ የማሽላ ክላስተር እና የሩዝ ክላስተር ተመልክቷል።
በነስረዲን ሐሚድ