በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ ኩራ ቀበሌ የሚገኙ 95 አርሶ አደሮች ከ150 ሔክታር በላይ በሆነ ማሳ ላይ ያመረቱትን የሩዝ ምርት በመሰብሰብ ላይ ናቸው።
አርሶ አደሮቹ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም በተስተካከለ የዝናብ ስርጭት እና ቀጣይነት ባለው የግብርና ባለሙያዎች ምክር ታግዘው ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ በክልሉ ለሩዝ ምርት ምቹ የሆነ 150 ሺ ሔክታር መሬት ተለይቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የመኸር ወቅት ከ41 ሺ ሔክታር በላይ በሆነ ማሳ ላይ ሩዝ መልማቱን ጠቁመው፤ ከዚህም ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
አርሶ አደሮች ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሩዝ አብቃይ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በክልሉ በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ተሰማ በበኩላቸው፤ በወረዳው ከ3 ሺ ሔክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ሩዝ እየለማ መሆኑን ገልፀው፤ ከቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበርም የአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር ፍላጎት እየተሟላ መሆኑን ተናግረዋል።
ተሞክሮውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በሰለሞን ባረና