Search

የ60 ዓመታት ግንኙነት ይበልጥ የጎመራበት የኢትዮ-ማሌዥያ ወዳጅነት

ሓሙስ ኅዳር 11, 2018 72

በባህል እና በሃይማኖት ብዝኃነቷ የምትታወቀው ማሌዥያ፣ በደቡብ ምስራቅ እስያ የምትገኝ እና ከፍተኛ-መካከለኛ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለች ሀገር ናት።
መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በሁለት የተከፈለ ባሕረ ገብ መሬት ሲሆን፣ ምዕራብ ማሌዥያ እና ሳባና ሳራዋክንን ባቀፈው ምሥራቅ ማሌዥያን ተብሎ ይጠራል።
ፌዴራላዊ አወቃቀር እና በምርጫ የሚቀያየር ዲሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥታዊ ንጉሣዊ የአስተዳደር ሥርዓትን ትከተላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ መሪ ነው፡፡ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ንጉሥ ያንግ ዲ-ፐርቱዋን አጎንግ ከዘጠኙ የማላይ ሥርወ መንግሥት አባላት መካከል የተመረጡ ናቸው።
የማሌዢያ ማኅበረሰብ በዋነኛነት ማላይዎችን፣ ቻይናውያን እና ህንዶች ከበርካታ የአገሬው ተወላጅ ጋር የተዋሃደበት ነው፡፡
የማሌዥያ ኢኮኖሚ በወጪ ምርቶች፣ በኢንዱስትሪ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ ፓልም ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርቶች ላይ የተመሰረተ ነው።
በማሌዥያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መነቃቃት በማሳየት ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር አድጓል።
ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት እ.አ.አ በጥር 1965 ሲሆን፣ በዚህ ዓመትን 60 ዓመት ሞልቶታል፡፡ በኢትዮጵያ ማሌዥያ ኤምባሲ ከ40 ዓመታት መቋረጥ በኋላ እ.አ.አ በመስከረም 23 ቀን 2025 በአዲስ አበባ ሥራውን ጀምሯል።
የኤምባሲው ዳግመኛ መከፈት ማሌዥያ ከኢትዮጵያ ግንኙነቷን ለማጠናከር እና አዲስ አበባ የመላው የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል ለመሆኗ ዕውቅና ለመስጠት ነው።
ኤምባሲው መከፈቱ በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን የሚከፍትም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባለፈው ዓመት በማሌዢያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
የሁለቱ መሪዎች ጉበኝት የሀገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ማሳያዎች ናቸው፡፡ መሪዎቹ በእነዚህ ጉብኝቶቻቸው በርካታ ጉዳዮችን አንስተው ተወያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ማሌዢያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ቁልፍ ዘርፎች ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ትስስር እያደገ ሲሆን፣ መሪዎቹ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሀገራቱ አብረው በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ኢንዶኔዥያ በገቢ እና ወጪ ንግድ፣ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ በፓልም ዘይት ላይ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ የምታጋራባቸው እና የሀገሪቱ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ሙዓለ ንወያቸውን የሚያፈስሱበት ጉዳዮች ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል፡፡
ግብርና፣ ነዳጅ፣ ቱሪዝም፣ ጤና እና ማዕድን ፍለጋ ማሌዥያ ከፍተኛ ልምድ ያካበተችበት እና ባለሀብቶቿ በትኩረት የሚመለከቷቸው ዘርፎች እንደሚሆን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በአዲስ አበባ እና ኳላላምፑር መካከል የበረራ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ በኳላላምፑር እና አበባ ከተማ አስተዳደሮች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
በለሚ ታደሰ