ኢትዮጵያ እና ማሌዥያ ተመሳሳይ ራዕይ የሚጋሩ ሀገራት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም በብሔራዊ ቤተመንግሥት ባደረጉት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ እና ማሌዥያ የተለያዩ አህጉራት ውስጥ ቢገኙም ሁለቱም ሀገራት በመከባበር፣ በመናበብ እና በጥንካሬያቸው ልብ ለልብ የሚግባቡ ሀገራት እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ማሌዥያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ድጋሚ መክፈቷን ያስተወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁለቱ ሀገራት የሚጋሯቸው እንደ ብዝኃነት እና አካታች ዕድገት ያሉ ተመሳሳይ እሴቶች ግን ከሁሉም የላቁ ናቸው ብለዋል፡፡
ምድረ ቀደምት እና የአፍሪካ መሰባሰቢያ የሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋዎችን፣ ባህሎችን እና እምነቶችን በአንድ አስተባብራ የኖረች ኅበረ ብሔራዊት መሆኗን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ማሌዥያም ኅብረ ብሔራዊነት በራዕይ ሲመራ እንዴት ጥንካሬ እንደሚሆን በተግባር ያስተማረች መሆኗን ተናግረዋል፡፡
"ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን መንፈስ ‘መደመር’ እንለዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ልዩነቶቻችንን ወደ ጥንካሬ በመቀየር አንዳችን ብቻችንን መሥራት የማንችላቸውን ነገሮች በኅብረት የምናሳካበት ነው" በማለት የመደመርን አሳቤ ገልጸዋል፡፡
በማሌዥያም በቀጣይነት፣ በብልፅግና፣ በፈጠራ፣ በመተማመን እና በፍቅር ላይ የተመሰረተ የጥንካሬ ራዕይ የሆነ "ማዳኒ" የተባለ የኅበረት እሳቤ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
"ማዳኒ" አንድ ዓይነትነት ሳይሆን አንድነት ወይም ኅበረት እንደሆነ እና ከፖሊሲ በላይም የጥንካሬ ምንጭነቱን ያረጋገጠ እሳቤ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡
"ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሀገራችን የብልፅግናን ራዕይ ሰንቃ ወጣቶቿን አስተባብራ ተአምር እየሠራች ባለችበት ወቅት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በጀመረችው የብልፅግና ጉዞ ባለፈው ዓመት የ9.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ሪፎርሟ ተአምር እየሠራች እንዳለችው ማሌዥያም "ሪፎርማሲ" ብላ በሰየመችው የተሃድሶ እንቅስቃሴዋ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣች መሆኗን ጠቅሰው፣ ሁለቱም የቀጣናቸው ወሳኝ ሀገራት መሆናቸው ሌላው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ መነሻነትም ሁለቱ ሀገሮች በሁሉም ዘርፍ አህጉራቱን ለማስተሳሰር እና ለቀጣይ የጋራ ዕድገት መንገድ የመክፈት ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBCdotstream #AbiyAhmedAli #Ethiopia #malasiya