Search

ኢትዮጵያ በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካን ድምጽ አሰምታለች - ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

እሑድ ኅዳር 14, 2018 91

ኢትዮጵያ በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካን ድምጽ በማሰማትና የአፍሪካን አጀንዳ ከፍ በማድረግ ውጤታማ ስራ መስራቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ተሳትፎ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በተካሄደው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ተጋባዥ ሆና መቅረቧ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተሳትፎ የራሷን እና የአፍሪካን አጀንዳዎች ከማቅረብ ባለፈ በጉባኤው ላይ ከሚሳተፉ መሪዎች ጋር ለሚደረገው የሁለትዮሽ ውይይቶች ዕድል የፈጠረላት መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

እንደዚህ ዓይነት መድረኮች በአንድ ጊዜ በርካታ ሥራዎች የሚሠሩባቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያም ይህን ዕድል በትክክል መጠቀሟን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት አሳታፊ እና አካታች እንዲሆን ለዚህ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ አቅም እንዳለ የራሷን ምሳሌ አንስታ፤ ለጉባኤው ማቅረቧን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

እንደ ፋይናንስ ሥርዓት ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካን ሚና ከፍ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ጥሪ መቅረቡንም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እየሠራች ያለችውን ሥራ ለጉባኤው ማቅረቧን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ዓለም እንደዚህ ዓይነቱን አፍሪካዊ መፍትሔ እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረቧንም ተናግረዋል፡፡

ሌላው ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ያነሳችው ጉዳይ የእዳ ማቃለል ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመው፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለእዳ የሚያወጡት ወጪ ለዕድገት መሰረተ ልማቶች ከሚያወጡት እየበለጠ በመሆኑ ጉዳዩ በትኩረት እንዲታይ መጠየቋን ገልጸዋል፡፡

በለሚ ታደሰ

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #G20Summit