ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ሲንጋፖርን ሲጎበኙ አቻቸው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ መጋበዛቸውን አስታውሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዎንግም ቃላቸውን በመጠበቃቸው አመስግነዋቸዋል፡፡
"ዓለምን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ሁላችንንም ይነካሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ችግሮቹን በጋራ እና በትብብር ለመፍታት ያደጉ ሀገራት ፊታቸውን ወደ አፍሪካ ማዞር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በዛሬው የዓለም ጂኦፖለቲካዊ የኢኮኖሚ ምህዳር የትኛው ከችግር ነጻ የሆነ ሀገር እንደሌለ ጠቁመው፣ ያደጉ ሀገራት ካፒታል እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዳላቸው ሁሉ አፍሪካም በርካታ በዚያ ወገን የማይገኙ ዕድሎች ስለሚገኙባት እነዚህ አቅሞች በማጣመር የተሻለች ዓለምን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ሲንጋፖር በፈጠራ እና በመልካም አስተዳደር ያመጣችው ለውጥ ኢትዮጵያ የምትማርበት እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በተቋማት ግንባታ፣ በአካታች ዕድገት እና በዲጂታል አስተዳደር ቀጣይነት ያለው ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗን ጠቅሰው፣ የጀመረችውን ጉዞ ለማፋጠን ከሲንጋፖር የምትቀስማቸው በርካታ ልምዶች እንዳሉ አውስተዋል፡፡
ዛሬ በነበረው የሁለትዮሽ ውይይቶች በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በበርካታ ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሥራት ከስምምነት መደረሱንም ጠቅሰዋል፡፡
የሲንጋፖር ባለሀብቶች በሎጂስቲክስ፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ አቪየሽን እና ቱሪዝም ዘርፎች ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም እንዲመለከቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማዕድንን እና የከተማ ልማትን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ሥራዎችን እየሠራች በመሆኑ ሲንጋፖር እነዚህን ዕድሎች እንድትመለከት ጠይቀዋል፡፡
ሲንጋፖር ክህሎት ባለው የሰው ኃይል እና በተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጧ የትኛውም ሀገር የሚመኘው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሷን ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድም አብሮ ለመሥራት ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡
ሲንጋፖር የላቀ ደረጃ ከደረሰችበት የአረንጓዴ ከተማ ልማትም ኢትዮጵያ ተጨባጭ ትምህርት ለመውሰድ ዘግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሲንጋፖር ጋር ያላትን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBCdotstream #Ethiopia #AbiyAhmedAli #Singapore #bilateralrelations