በኢትዮጵያ እና በሲንጋፖር መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ትስስር አፍሪካን እና ደቡብ ምሥራቅ እስያን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቴክኒካዊ የዕውቀት ልውውጥ ማስተሳሰር ላይ ያተኮረ ነው።
በ2024 ሃምሳ አምስተኛ ዓመቱን ያከበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁን ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ እየገባ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሲንጋፖር ጉብኝት በማድረግ ከአቻቸው ሎውረንስ ዎንግ ጋር ተወያይተዋል። ጉብኝቱ ለላቀ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካዊ ትብብር መንገድ ከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ እያደረጉት ያለው ጉብኝት ወደ አፍሪካ ሀገር ያደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አጉልቶ ያሳየ ሆኗል።
የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ሲንጋፖር በልማት እና አስተዳደር ላይ ያላትን ዕውቀት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትሳተፍበትን መንገድ የሚያመቻች ነው።
ሲንጋፖር በሲቪል አቪዬሽን፣ በውኃ አስተዳደር፣ በወደብ አስተዳደር እና በአመራር ረገድ ያካበተችውን ጠንካራ ልምድ ለኢትዮጵያ እንድታካፍል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ ለምታዘጋጀው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ሲንጋፖር በካርቦን ንግድ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ ያላትን ልምድ ልታካፍል የመግባቢያ ስምምነት (MOU) ተፈርሟል።
ሲንጋፖር ይፋዊ አጠራሯ የሲንጋፖር ሪፐብሊክ ሲሆን፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኝ ደሴት እና የከተማ ግዛት ናት። ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ቢኖርባትም ስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድር ያላት ስትሆን፣ ይህን አቅሟንም ወደ ዕድል መቀየር ችላለች። የተፈጥሮ ሀብት እና ውኃ የሌላት ብትሆንም፤ በጠንካራ ሕዝቧ ጥረት ከዓለም ቀዳሚ ኢኮኖሚ ከገነቡ እና በንጹህ ውኃ ተደራሽነት ከሚጠቀሱ ሀገራት አንዷ ሆናለች።
ሲንጋፖር ከማሌዥያ ሙሉ ነጻነቷን ያገኘችው እ.አ.አ በ1965 ነበር። አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 736.3 ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን፣ በ6.1 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት በዓለማችን ከሚገኙ ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግት ካለባቸው ሀገራት የመጀመሪያዋ ናት።
ይህን ዓለምን ያስደነቀ ለውጥ ያመጣችው መሪዎቿ በቀረጹት እና በቁርጠኝነት በተተገበሩት ገቢር-ነበብ (pragmatic) የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ነው። ስታርታፕ፣ ካፒታል ገበያ እና ቴክኖሎጂ ከሀሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንቶች መካከል ናቸው።
በተዓምራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቷ፣ በዜጎቿ ከፍተኛ የሕይወት ጥራት፣ በፖለቲካ መረጋጋት እንዲሁም ለፋይናንስ፣ ለንግድ እና ለቴክኖሎጂ ዋና ማዕከል በመሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትጠቀሳለች።
በአንድ ትውልድ ከዝቅተኛ ገቢ ወደ የዳበረ እና ከፍተኛ ገቢ ኢኮኖሚ (high-income economy) የተሸጋገረች፣ በዓለም ላይ ለሁሉም ክፍት እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ያላት ተዓምረኛ ሀገር ናት።
በጅምላ ምርት ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ ባላቸው የላቁ ምርቶች ላይ ተመስርቶ ኤሌክትሮኒክስ፣ የባዮ ሜዲካል ምርቶች እንዲሁም ኬሚካሎች እና ፔትሮኬሚካሎችን የያዘው የኢንዱስትሪ ዘርፏ 24.8 በመቶ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ይይዛል።
ፋይናንስ፣ ሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርትን እንዲሁም ሙያ እና ቱሪዝምን ያካተተው የአገልግሎት ዘርፏ ደግሞ 75.2 ከመቶ ኢኮኖሚዋን ይደግፋል።

የሀገር ውስጥ ምርቷ ለዜጎቿ ሲከፋፈል (GDP Per Capita) በ156 ሺህ 970 ዶላር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ሀብት እና የመግዛት አቅም ይዛ አንደኛ ደረጃ ላይ ናት። በጣም አነስተኛ ሙስና ካለባቸው ሀገራትም 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የተፈጥሮ ሀብት በተለይም የውኃ እጥረት ቢኖርባትም ጨዋማ ውኃን በማጣራት እና ውኃን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል (NEWater) ከአራት ከፍተኛ የውኃ ማጠራቀሚያዎቿ ጥራት ያለው ውኃ ታገኛለች።
80 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የሚኖረው በቤቶች እና ልማት ቦርድ (HDB) በሚተዳደሩ ከፍተኛ ጥራት ባላቸው እና ድጎማ በሚደረግላቸው የሕዝብ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነው።
ትምህርትን፣ የጤና እንክብካቤን እና መሠረተ ልማትን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ ማኅበራዊ ልማት አመልካቾች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሲንጋፖር በኅብረ ብሔራዊነት የምትታወቅ ሀገር ናት። በሕገ መንግሥቷ በይፋ እውቅና ያገኙት ሦሰት ትላልቅ ዝርያዎች ቻይና 74.3 በመቶ፣ ማላይ 13.5 በመቶ እንዲሁም ሕንድ 9 በመቶ ሲሆኑ፣ የሌሎች መብትም በሕገ መንግሥቷ የተጠበቀ ነው። ሲንጋፖር ከአንድ በላይ ቋንቋዎችንም ትጠቀማለች። እንግሊዝኛ የአስተዳደር፣ የንግድ እና የትምህርት ቋንቋ ነው። ማላይ፣ ብሔራዊ ቋንቋ ሲሆን፣ ማንዳሪን እና ታሚል ጎን ለጎን አገልግሎት የሚሰጡ ቋንቋዎች ናቸው።
ሲንጋፖር የሃይማኖት ብዝኃነት ካለባቸው የዓለማችን ሀገራት አንዷ ናት። ከሕዝቧ መካከል 31.1 በመቶ ቡድሂዝም፣ 20 በመቶ ሃይማኖት የሌለው፣ 18.9 በመቶ ክርስትያን፣ 15.6 በመቶ ሙስሊም፣ 8.8 በመቶ ታኦይዝም፣ 5 በመቶ ሂንዱይዝም እንዲሁም 0.6 በመቶ ሌሎች ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ናቸው። የተከታዮቹ ቁጥር ከግምት ሳይገባ ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል ናቸው።
የመንግሥት ሥርዓቷ በርዕሰ ብሔር እና በርዕሰ መንግሥት የተዋቀረ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ርዕሰ ብሔር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕሰ መንግሥት ናቸው።
መደበኛ ምርጫ የሚደረግበት መድበለ ፓርቲ ሥርዓት የምትከተል ሲሆን፣ ከ1959 ጀምሮ የሕዝባዊ እርምጃ ፓርቲ (PAP) የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ነው።
ሲንጋፖር ከተፈጥሮ ጋር ታግላ እዚህ ከፍተኛ ደረጃ ጥራት ያለው የኑሮ ደረጃ ላይ የደረሰችው በጠንካራ የሰው ኃይሏ ቢሆንም፤ አሁን አሁን ወጣት ኃይሏ እየቀነሰ በመምጣቷ ስጋት ውስጥ ገብታለች።
በለሚ ታደሰ
#eccdotstream #Ethiopia #Singapore