Search

የመደመር መንግሥት ሕዝብን ያዳምጣል፣ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ቅዳሜ ኅዳር 27, 2018 74

ዛሬ ከማለዳ አንስቶ ከነዋሪዎቻችን ጋር ሰፊ ውይይቶችን አካሂደናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ውይይቶቹ በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በስፋት መካሄዳቸውን ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች ላይ ከነዋሪዎቻችን ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎች እና አስተያየቶች በተግባር የተሰጡ ምላሾች፣ እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን አስመልክቶ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደራችን ከፍተኛ አመራሮችና ሚኒስትሮች መድረኮቹን በመምራት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ የቤት ስራም ወስደዋል ሲሉ አመላክተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማችን በተለያዩ የልማት ሥራዎች አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡት መንግሥትና ሕዝብ አንድ ሆነው በመቀናጀትና በመናበብ ሊፈጽሟቸው በመቻላቸው መሆኑን ገልጻል።
የመደመር መንግሥታችን ሕዝብን ያዳምጣል፣ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።
ዛሬም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የተሰሩ በርካታ ሥራዎችን እና የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ እንዲሁም የሕዝብን ተሳትፎ ይበልጥ በሚያረጋግጡ ቀጣይ የጋራ ዕቅዶች ላይ እንደ ወትሮው ከነዋሪዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ያገኘንበት ፍሬያማ የውይይት መድረክ ነበር ሲሉ ጠቁመዋል።
ውድ ነዋሪዎቻችን፣ ለሰጣችሁን ገንቢ አስተያየት፣ ለነበራችሁ ከፍተኛ ተሳትፎ፣ ለሰጣችሁን ውድ ጊዜ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል።
በቀጣይም ይበልጥ ተቀራርበን መሥራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።