የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ለተፈናቃዮች ድጋፍ የሚውል የ206 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባ።
በጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ሪም አላባሊ ራዶቫን የተመራ ልዑካን ቡድን በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ጋር ተወያይቷል።
ልዑካኑ ዛሬ በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሀገራቱን የረዥም ጊዜ የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር በሪፎርም ላይ ያተኮረ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የልማት ትብብሮችን በማሳደግ የሁለቱን ሀገራት ዘላቂ ትብብር ማጠናከር ላይ እንደምትሠራ የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትሯ ሪም አላባሊ ራዶቫን ተናግረዋል።
ልዑካኑ እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2027 የሚቆይ የሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ-ጀርመን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በኢትዮጵያ ወገን የጀርመን መንግሥት ላሳየው ጠንካራ የልማት ትብብር ድጋፍ ምስጋና የቀረበ ሲሆን፣ የሀገራቱ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ማሻሻያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለጀርመን ልዑካን መረጃ በመስጠት መንግሥት የሪፎርም ትግበራውን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት በአጽንኦት ገልጸዋል።
የገበያን አሠራር ማሻሻል፣ የሎጂስቲክስ እና የንግድ ፋሲሊቲዎችን ማሳደግ እና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል የድጋፉ አካል እንደሆነም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ከማመንጨት እስከ ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ያለው የኢነርጂ ልማት የፋይናንስ ክፍተትን ለመሙላት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊነት አፅንዖት እንደተሰጠው አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋያቸውን የሚያፈስሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።
የሁለቱም ሀገራት ልዑካን የረዥም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የልማት ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ በማረጋገጥ ስብሰባቸውን አጠናቅቀዋል።
በለሚ ታደሰ