Search

በቀይ ባሕር ንግድን፤ አሁን ደግሞ ዕውቀት የሚገበያዩት ኢትዮጵያ እና ሕንድ

ቅዳሜ ታኅሣሥ 11, 2018 94

ኢትዮጵያ ሲባል ብዙ መልኮች የሚታያቸው ቢኖሩም ኢትዮጵያ ዛሬ በብዙ መንገድ ሌላ ነች፤ ፊቱን ያዞረባት ዓለም በሰልፍ እንዲጎበኛት የሚያስገድድ የለውጥ ባቡር ውስጥ ነች።

ከአውሮፓ እስከ እስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መሪዎች የጎበኟት ኢትዮጵያ በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንድትሳተፍ የምትጋበዝ በዚያም የነበሩ የዓለም ዘዋሪ መሪዎች ሊያወያዩአት ሰልፍ ይዘው የሚጠብቋት መሆኗ በይፋ በቅርቡ የታየ ሐቀ ሆኗል።

ሰሞኑን ደግሞ የጉብኝት ተራው የ1.4 ቢሊዮን ህዝብ መኖሪያዋ ህንድ ሆናለች። ለዚህም ነው የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በዲፕሎማሲው መስክ ብዙ ጊዜን ይፈጅ የነበረውን የጉብኝት ሂደት በቀላሉ አልፈው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ መገኘት ምስጢር ቀላል የዲፕሎማሲ ጉብኝት ብቻ አይደለም። ገብኝቱ ታሪክን የሚጠቅስ፣ ስትራቴጂን የሚያጠናክር እና የደቡብ ክፍለ ዓለም የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚበይንም ጭምር ነው።

በእርግጥ ከዲፕሎማሲያዊ ተግባራቱ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬድራ ሞዲ በኢትዮጵያ እንዲገኙ እጅግ ማራኪ ታሪኳን እና በዓለም ላይ ከሚገኙ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች መገኛ መሆኗ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህን አይነቱን ማንነት ሁለቱ ሀገራት የሚጋሩት መሆኑ ደግሞ ሌላኛው መልክ ነው።

ቀደምት የሰው ዘር መገኛ የሆነችው እና የዓለም የስልጣኔ ቁንጮ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ዳግም ወደ ስልጣኔ መንገዷ እየተመለሰች በአራቱም ማዕዘን የዓለምን ቀልብ እየሳበች ትገኛለች።

ቅኝ ግዛትን ተዋግታ ነጻነቷን ከማስከበር ባለፈ የአፍሪካ ነጻነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ ከትላንት እስከ ዛሬ ፍትሐዊ የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር እያደረገችው ያለው ጥረት እንደ ህንድ አይነቶቹን ሀገራት ቀልብ የሚስብ ታሪኳ ሆኗል።

በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ያለችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ፣ ውበቷ እየፈካ የመጣቸው አዲስ አበባ ደግሞ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ዋና ከተማ ነች።

ከመንግሥታቱ ማኅበር እስከ መንግሥታቱ ድርጅት ፍትሃዊ የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር ድምጿን ከማሰማት ቦዝና የማታውቀው ኢትዮጵያ በ2024 የደቡብ ከፍለ ዓለም ጥምረት የሆነውን ብሪክስን ተቀላቅላለች፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ፍትሃዊ የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር እየሠራች ያለችው እና የብሪክስ መሥራች የሆነችው ህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ15 ዓመታት በኋላ መሪዋ ናሬንድራ ሞዲ የመጀመሪያው ጉብኝት በኢትዮጵያ አድርገዋል።

ህንድ በ2026 የብሪክስን ሊቀ-መንበርነት ትረከባለች፤ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር የናሬድራ ሞዲ ጉብኝት ኢትዮጵያ እና ህንድ በጥምረቱ ውስጥ የሚኖራቸውን መጻኢ ጊዜ የሚያመላክት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የህንድ እና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ላደረጉት ጥረት እና የኢትዮጵያን የክብር ኒሻን የተሸለሙ የመጀመሪያው የዓለም መሪ ሆነዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ አዲስ አበባ ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው መቀበላቸው ከዕይታ እና ከጋዜጣዊ መግለጫዎች በላይ ትርጉም ያለው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በኢትዮጵያ በህዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ሥብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ የህንድ ብሔራዊ መዝሙር በሆነው "ቫንድ ማታራም" እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር  "የዜግነት ክብር" መካከል ያለውን ተመሳሳይነት አመላክተዋል።

ሁለቱም መዝሙራት ሀገራቸውን በእናት እንደሚመስሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፣ "መዝሙሮቹ በቅርስ፣ በባህል፣ በብሔራዊ ውበት እንድንኮራ እና እናት ሀገርን እንድንጠብቅ ያነሳሱናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የህንድ ግንኙነት ወደ 2 ሺህ ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ነው፤ አውሮፓ ራሷን ባላወቀችበት ወቅት የህንድ ነጋዴዎች ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ወደቦች ይጓዙ ነበር።

ሀገራቱ ቅመማ ቅመም፣ ሐር እና ጥጥ በወርቅ እና በዝሆን ጥርስ ተገበያይተዋል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዕውቀትን ይገበያዩ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል።

ኢትዮጵያውያን የቅኝ ግዛት ጫናዎችን ይቃወሙ በነበሩባቸው ወቅቶች ህንዶች ከጎናቸው ነበሩ፤ ታሪካዊ ግንኙነታቸው እጅግ ሰፊ እና በጽኑ መሰረት ላይ የታነጸ ነው።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የህንድ ወታደሮች በአፍሪካ ውስጥ ተዋግተዋል፤ የህንድ መምህራን በኢትዮጵያ ውስጥ ትውልድን ሲያንጹ ኖረዋል።

በመሆኑም የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት አዲስ ጓደኝነት መፍጠር ሳይሆን ነባሩን ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማሳደግ ነው።

በደቡብ እስያ የምትገኘዋ ህንድ በቀጣናዋ ፈጣን እድገት እያሳየች የምትገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘዋ ኢትዮጵያ ደግሞ የቀጣናዋ እና የአፍሪካ አስተሳሳሪ እና ፈጣን ለውጥ ውስጥ ያለች ነች፡፡

ህንድ የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ትልቋ የንግድ አጋር ነች፡፡ 650 የሚሆኑ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ወስጥ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርገዋል። እነዚህ ኩባንያዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ለኢትዮጵያውያን ፈጥረዋል።

ህንድ ለባቡር መሰረተ ልማት፣ ኤሌክትሪክን ለማዳረስ እና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የሚውል የ1 ቢሊዮን ዶላር የረጅም ጊዜ ብድር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች፡፡

ሁለቱ ሀገራት በዲጂታል፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በመከላከያ እና በቱሪዝም ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

በለሚ ታደሰ