የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው ሕገ-ወጥ ስደት አሁንም ድረስ አሳሳቢነቱ የቀጠለ ሲሆን፣ ዜጎች የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሚያደርጉት አደገኛ ጉዞ አማካኝነት ለከፋ እንግልት እና ስቃይ እየተዳረጉ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀደም ባለ ጊዜ በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ የዜጎቻችን ክብር የሀገራችን ክብር ነው፤ በመሆኑም ወጣቶቻችን በሰው ሀገር ከሚደርስባቸው መከራና ስቃይ ወጥተው በኢትዮጵያ ሰርተው እንዲለወጡና ክብራቸው እንዲጠበቅ ማድረግ የሁላችንም ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ማለታቸው አይዘነጋም።
የአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኅበር የተሀድሶ ማዕከል ኃላፊ ወይዘሮ ሔለን ዘገየ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ሕገ-ወጥ ስደት በየጊዜው በርካታ ወገኖቻችንን ለአካል ጉዳትና ለሕይወት መስዋዕትነት እየዳረገ ይገኛል።
የሕገ-ወጥ ስደት አስከፊነት በአሁኑ ወቅት መጨመሩንና የስደተኞች ቁጥርም በየወቅቱ እያደገ መምጣቱንም አስረድተዋል።
ስደተኞች በጉዞ ወቅትና በደረሱባቸው ሀገራት የሚያጋጥማቸው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት አስከፊ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ሔለን፣ ዜጎች ለዓመታት የለፉበትን ገንዘባቸውን ከማጣታቸው ባለፈ ለከፍተኛ የጤና መታወክ እንደሚዳረጉና በተለይም ሴቶች ለተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታትም የመደመር መንግሥት ለስደት ተመላሾች ልዩ ትኩረት በመስጠት የሥራ እድል በማመቻቸትና ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለያዩ የአረብ ሀገራት እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የማመለስ ተግባርም በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኅበር የተሀድሶ ማዕከልም ለስደተኞች ተመላሾች ልዩ እንክብካቤ በማድረግ የስነ-ልቦና ምክር የሚሰጥ ሲሆን፣ የሕክምና እና የሙያ ስልጠናዎችን እያቀረበ መሆኑንም አንስተዋል።
በአጠቃላይ ይህንን የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፈው ሕገ-ወጥ ስደት ለመግታትና ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም ኅብረተሰቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አመላክተዋል።
በሜሮን ንብረት