Search

ሕዝባዊ የውይይት መድረኮቹ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤታማነት የተንጸባረቀባቸው እና ተጨማሪ የመልማት ጥያዌዎች በነጻነት የተነሱባቸው ናቸው - የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

እሑድ ታኅሣሥ 12, 2018 35

በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተካሄዱት ህዝባዊ ውይይቶች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤታማነት የተንጸባረቀበት እንዲሁም ተጨማሪ የመልማት ጥያዌዎች በነጻነት የተነሱበት መድረክ እንደነበር የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በባህርዳር ከተማ በነበረው ሕዝባዊ ውይይት ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፤ በመድረኩ የነበሩ ሃሳቦችና የተገኙ ግብዓቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸውም የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በውይይት መድረኩ ያሳዩት የነቃ ተሳትፎ የሚደነቅ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ሕዝቡን በማዳመጡ ተግባራዊ የተደረጉ እቅዶች ህዝቡ ጋር ውጤት እያመጣ መሆኑን ያየንበት ነው ብለዋል፡፡
የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤታማነት የተንጸባረቀበት እንዲሁም ተጨማሪ የመልማት ጥያዌዎች በነጻነት የተነሱበት መድረክ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ይህም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩንና ወደ ፊትም ይበልጥ እንደሚጠናከር የታየበት ነው ሲሉም ገልጸዋል ሚኒስትሯ፡፡
በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ መድረክ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በውይይቱ ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅና ጉልበት የሚሆኑ ሐሳቦች በስፋት መነሳታቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በርካታ ሰዎች ማለትም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና የመንግሥት ሰራተኞች በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎች የተሠሩትን ሥራዎች ማድነቃቸውንና እንዲስተካከል የሚፈልጉትንም መጠቆማቸውን ነው የጠቀሱት።
የጉባ ብሥራቶችን ጨምሮ የባሕር በር ጉዳይ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሳኩ የሚጠይቁ ሐሳቦች በስፋት መስተጋባታቸውንም ተናግረዋል።
እነዚህ አስተያየቶች ደግሞ የበለጠ ቁጭት እና ተነሳሽነት የሚፈጥሩ በመሆናቸው፤ ለቀጣይ ሀገራዊ ሥራዎች ስንቅና ጉልበት ስለሚሆኑ በግብዓትነት ይወሰዳሉ ሲሉም ገልጸዋል።