"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሻገረ ስኬታማ ጉዞ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ይገልጻሉ።
ባለፉት ዓመታት የተዘረጋው የዲጂታል አሠራር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት በማዘመንና የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ ረገድ ታላቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የዲጂታል መሠረተ ልማቱ የሕዝብ ትስስርን በማጠናከር፣ አገልግሎትን በማዘመን፣ የንግድ ሥርዓትንና የመንግሥትን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ትልቅ እምርታ የታየበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራራሉ።
ይህ ሥርዓት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግር መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ የዲጂታል ሽግግር ሒደት ውስጥ የወጣቶቻችን ሥነ-ልቦና፣ አስተሳሰብና አሠራር መቀየሩን ነው የገለጹት።
በዚህ በተቀየረ እሳቤ፣ ሥርዓትና አጠቃቀም መሠረት ደግሞ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር የግድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም አስገንዝበዋል።
ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተደረገውን አዲስ የሽግግር ምዕራፍ ታሳቢ በማድረግም፣ ከሳምንታት በፊት ስትራቴጂው በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አቶ ተመስገን አስታውሰዋል።
አዲሱ ስትራቴጂ በሁሉም ዜጋ ጥረትና ትብብር የተጀመሩ የዲጂታል ውጥኖች በፍጥነት የሚስፋፉበትና ተናባቢ የዲጂታል ሥነ-ምኅዳር የሚገነባበት ወሳኝ ፍኖተ ካርታ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ዘላቂ የሆነ የዲጂታል እመርታን ከማምጣት ባለፈ፣ በሥርዓት የተደገፈ ሀገራዊ ትራንስፎርሜሽንን የሚያረጋግጥ ይሆናል።
ይህ አዲስ ምዕራፍ ዜጎችን ማዕከል ያደረገ መንግሥታዊ ሥርዓት በእጅጉ የሚጎለብትበት፣ ሁሉን አቀፍ አካታች የዲጂታል አገልግሎቶች የሚቀርቡበትና ሉዓላዊነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ሥርዓት የሚበራከትበት እንደሆነም አስረድተዋል።
የውስጥ ፈጠራን በማበረታታትና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በማሳለጥ፣ ወደምንመኘው ሁለንተናዊ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን አውድ ሆኖ እንደሚያገለግልም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ