ዛሬ በሸገር ከተማ ለቡ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢኩስታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጎብኝቻለሁ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ልማት የምታደርገው አስተዋጽዖ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀየረ ነው ብለዋል።
በትምህርት፣ በጤና፣ በመጠጥ ውኃ ልማት እና በወጣቶች የቴክኒክ ሥልጠናዎች የምታደርጋቸው የልማት ድጋፎች ለሀገራችን የብልፅግና ጉዞ አበርክቷቸው ታላቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዛሬ የጎበኘነው ተቋም በተለይም በሕክምናው ዘርፍ የሀገራችንን የመመርመርና የማከም ዐቅም ያሳድጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሁሉም በላይ የተቋሙ ንጽሕና እና ጽዳት ለብዙ ተቋማት ምሳሌ ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል።
አስፈላጊ ሁኔታዎች ተሟልተው በቶሎ ሁለንተናዊ አገልግሎቱን እንዲጀምር በመንግሥት በኩል የሚፈለጉትን ድጋፎች እናደርጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
ለተቋሙ የሚሆን መሬት የሰጠውን የኦሮሚያ ክልልን፤ እንዲሁም ተቋሙን በዘመናዊ መሣሪያዎች ለማደራጀት ያገዙትን ሁሉ በዚሁ አጋጣሚ አመሰግናለሁ ብለዋል።