ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ዲጂታል አማራጭ በሀገራችን ስለመኖሩ ስንቶቻችን እናውቃለን?
የጤና ፈርስት ‘ቴሌ ሜድስን’ በዚህ ተጠቃሽ ነው።
በ1 ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ፣ ከ10 ሺህ በላይ ታካሚዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን የጤና ፈርስት ቴሌ ሜድስን መስራች ወጣት አብርሃም አሰፋ ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ተናግሯል። ከታካሚዎቹ አብዛኛው በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ናቸው ብሏል።

የስልክ ሕክምና (‘ቴሌ ሜድስን’) ታካሚዎች በአጭር የመደወያ ቁጥር በድምጽ አሊያም በዘመናዊ (ስማርት) ስልክ ኢንተርኔትን በመጠቀም በቪዲዮ የሚፈልጉትን ስፔሻሊስት በደቂቃዎች ውስጥ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት ነው።
በዚህም ባለሙያው ከታካሚው ሙሉ የጤና መረጃ ከወሰደ በኋላ በታካሚው አቅራቢያ ከሚገኝ ቤተ-ሙከራ ጋር በኦንላይን መረጃ ተለዋውጦ ምርመራ እንዲያካሂድ ያደርጋል።
ከዚያም ባለሙያው የምርመራውን ውጤት ከቤተ-ሙከራው በኦንላይን ተቀብሎ አስፈላጊውን መድኃኒት በማዘዝ ታካሚው በአቅራቢያው ካለ መድኃኒት ቤት ገዝቶ እንዲወስድ ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በጤና ፈርስት በኦንላይን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ወጣት አብርሃም ይናገራል።
ከኢትዮጵያ አልፎ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ምስራቅ አፍሪካ ያሉ ዜጎች በዲጂታል አማራጭ የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት እንደሚጠቀሙም ነው የገለጸው።
ለማዋለድ አገልግሎት እና ቀዶ ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ከበድ ያሉ ሕክምናዎች በአካል ወደ ጤና ተቋም መሄድ ግድ ቢሆንም፤ ለምዝገባ እና ወረፋ ለመያዝ ‘ቴሌ ሜድስን’ን መጠቀም ይቻላል።
‘ቴሌ ሜድስን’ በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ቢመጣም፤ ተደራሽነቱ ይበልጥ እንዲሰፋ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የመደመር መንግሥት በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂው ሁሉም ዜጎች ከቤታቸው ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበትን እኩል ዕድል ለማረጋገጥ ብሎም በዜጎች እና በተቋማት መካከል መተማመንን ለመገንባት እየሠራ ይገኛል።
በየተመኙሽ አያሌው
#EBC #ebcdotstream #DigitalEthiopia #telemedicine