ኢትዮጵያ ያለ ሕጋዊ መሠረት ያጣችውና የትውልድ የህልውና ጥያቄ የሆነው የባሕር በር ተጠቃሚነት እስኪረጋገጥ ድረስ የማይረግብ የሁልጊዜም አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ገለጸ።
ወደ ኋላ ሦስት አሥርት ዓመታትን ስንመለከት፣ ስለ ባሕር በር ማውራት እንደ ትልቅ ኃጢአት እና ወንጀል የሚቆጠርበት፣ ‘ስንፈልግ ወደብን እንገዛዋለን’ የሚል የተሳሳተ እሳቤ የሰፈነበት ዘመን እንደነበር አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ያስታውሳል።
የባሕር በር ለሀገር ያለውን ወሳኝ አስፈላጊነት ለመረዳት የብሔራዊ ጥቅምን ስሜት መላበስ እንጂ ሊቅ መሆንን እንደማይጠይቅም ያነሳል።
አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ፣ በወቅቱ የነበረውን የታሪክ ስብራትና የኢኮኖሚ ጉዳት በመረዳት፣ ቁጭቱን “የባሕር በር” በተሰኘ ፊልሙ ለመግለጽ ጥረት አድርጎ እንደነበር ገልጿል።
ይህ ፊልም ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለምን አጣች? እንዴትስ በባለቤትነት ልታገኝ ትችላለች? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚሞግትና የወደብ ኪራይ ከገንዘብ በላይ የኢትዮጵያ የደኅንነትና የህልውና ምስጢር መሆኑን የሚያመላክት እንደነበር ያስረዳል።
ይሁን እንጂ ፊልሙ አስፈላጊውን የሙያ ቅደም ተከተል አልፎ ለሕዝብ ዕይታ ዝግጁ ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው መንግሥት እንዳይታይ ተደርጎ እንደነበር ይናገራል።
የባሕር በር ይገባናል የሚለው ጥያቄ አጀንዳ እንዲሆን ጥናትና ምርምር አድርጎ የሠራው ፊልም እንዳይታይ ከመታገዱ ባለፈ፣ በእርሱና በቤተሰቡ ላይ ለደኅንነቱ አስጊ የሆኑ ማስፈራራቶች በመድረሳቸው ሀገሩን ጥሎ ለመሰደድ መገደዱንም ያስታውሳል።
“ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች ኢትዮጵያዊ ናቸው ወይ? እስኪባል ድረስ ጉዳዩ ይከነክነኝ ነበር” የሚለው አርቲስት ጥላሁን፣ ለአንድ ዓመት በስደት ከቆየ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በሙያው እያገለገለ መሆኑንም ይገልጻል።
ዛሬ ላይ የባሕር በር ጉዳይ የትውልዱ ጥያቄና የትኩረት ማዕከል ሆኖ በመመልከቱ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማው የገለጸው አርቲስቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት በልባቸው የነበረውን የረጅም ጊዜ የባሕር በር ጥያቄ አንስተው ለተግባራዊነቱ እየሠሩ መሆናቸውን ማየቱ “ዕድለኛ ነኝ” እንዲል እንዳደረገውም ተናግሯል።
አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ፣ ምንም እንኳ የሥራ ባልደረቦቹና አድናቂዎቹ “የባሕር በር” ፊልም አሁን ላይ ለሕዝብ እንዲቀርብ ቢጠይቁትም፣ እርሱ ግን ከገንዘብና ከዝና በላይ የሀገር ክብርና ጥቅም እንደሚቀድም በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት በተጨባጭና በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪረጋገጥ ድረስ ፊልሙን ላለመልቀቅ መወሰኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያውያንም የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ አጀንዳው ሳይረግብ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል። ሁሉም ዜጋ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በጋራ እንዲቆምም አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ጥሪውን አቅርቧል።
በአፎሚያ ክበበው እና በሔለን ተስፋዬ