Search

እንግልትን ያስቀረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

እሑድ ታኅሣሥ 19, 2018 146

የመደመር መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ለዜጎች ምቹ ለማድረግ በጀመረው ጥረት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በተለያዩ ከተሞች እያስፋፋ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ከንቲባ ባላቸው ከተሞች ላይ ቢያንስ፣ ቢያንስ አንድ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሊኖር እንደሚገባ ማመላከታቸው አይዘነጋም።
በዚሁ መሠረት ከ250 በላይ በሚሆኑ ከተሞች ማዕከላቱን ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፤ እስከ መጪው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 79 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን ለመክፈት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አመላክቷል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ መድረኮች እንደተናገሩትም፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሙስናና ለእንግልት የሚዳርጉ አሠራሮችን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ የሚቀይር ነው።
አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ፣ ባለጉዳዩ አገልግሎቱን አግኝቶ እስኪወጣ ድረስ ያለው ሰዓት በሙሉ በሲስተም የሚመዘገብና ክትትል የሚደረግበት መሆኑ ግልጽነት ያለው አሠራር ለማስፈን እንደሚረዳም በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ይህ የተቀላጠፈ አሠራር የአገልግሎት ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ፣ ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ የማዕከላቱ ተጠቃሚዎች ያስረዳሉ።
ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ዜጎች ምቹ አገልግሎት እየቀረበበት የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በውጤታማነቱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ተገልጋዮች ይገልጻሉ።
ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ውጤታማነቱ የተረጋገጠው አዲስ መሶብ፣ ቴክኖሎጂን ከመሠረታዊ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት ነዋሪዎች ሳይጉላሉ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑ ይነገራል።
ይህንኑ ስኬታማ ተሞክሮ በማስፋፋትም የመንግሥት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች ለማቅረብ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም ተገልጋዮች ይገልጻሉ።