Search

በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ 1 ሺህ 300 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ታኅሣሥ 21, 2018 156

ባለፉት አምስት ወራት በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ1 ሺህ 300 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና ለመከታተል ምን እየተሠራ ነው? በማለት ላቀረቡላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዜጎች በውጭ ሀገራት መብታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ የመደመር መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው ከፍተኛ ክትትል ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 300፣ እንዲሁም በሳውዲ ዓረቢያ የነበሩ 26 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጸዋል።
ዜጎቹን ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ፤ አሁንም በደላሎች ያልተጨበጠ መረጃ የሚታለሉ ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ እየሄዱ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። በመሆኑም ዜጎች ለሕይወት አስጊ ከሆኑ ሕገ-ወጥ ጉዞዎች ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሄደው እንዲሠሩ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። በተለይም በአረብ ሀገራት በሚገኙ ቆንስላዎች ዜጎችን የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች ተመድበው የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
ከአሠሪዎቻቸው ጋር ችግር ለሚገጥማቸው ዜጎች የሕግ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።
 
በባዬ ሙላት