ሊጠናቀቅ የሰዓታት ዕድሜ በቀሩት የፈረንጆች 2025 ዓመት የዓለምን ትኩረት ስበው ከነበሩ ዜናዎች መካከል አንዱ የዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ መንበረ ሥልጣን መመለስ ነበር።
በጃንዋሪ 20 ቀን 2025 ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው በደማቅ እና ታሪካዊ ሥነ ሥርዓት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ይህ የዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ መንበረ ሥልጣን መመለስ በአሜሪካም ሆነ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚሁ እየተገባደደ ባለው ዓመት የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ግንባታ በማጠናቀቅ የመቻል አቅሟን ለዓለም አሳይታበታለች።
ኢትዮጵያውያን ከልጅ እስከ አዋቂ የተሳተፉበት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ በስተመጨረሻም የኢትዮጵያን ታላቅነት ባሳየ መልኩ ተጠናቅቆ ለምርቃት የበቃበት ዓመት ነበር።

በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለ ጉዳዩ በስፋት ሲዘግቡ የኢትዮጵያውያንን የመቻል አቅም በጉልህ አሳይተዋል።
ዶቼ ቬለ (DW) ግድቡ ያለ ውጭ ዕርዳታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ እና ጉልበት መገንባቱን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ልብ ያስተሳሰረ ታላቅ ፕሮጀክት ሲል ዘግቦታል።
ሮይተርስ በበኩሉ "በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በእጥፍ ያሳድገዋል" ሲል የገለጸ ሲሆን፤ ፍራንስ 24 ደግሞ "ኢትዮጵያ ሚሊዮኖችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ግዙፍ ግድብ ግንባታ አጠናቀቀች" ሲል ዘግቧል።
በተጨማሪም ግድቡን "የኢትዮጵያውያን ኩራት" በማለት ከገለጸው ግዙፉ የዜና አውታር ቢቢሲ (BBC) ጀምሮ "ኢትዮጵያውያን ተስፋን የሰነቁበት በአፍሪካ ግዙፍ ግድብ ተገንብቶ ተጠናቀቀ" በማለት እስከገለጸው አሶሺየትድ ፕሬስ (AP) ድረስ ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከፍተኛ የዜና ሽፋን ሰጥተዋል።
2025 የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ፉክክር የተጠናከረበት ዓመትም ነበር። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፈረንጆቹ 2017 ባደረጉት ንግግር "በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቀዳሚ የሆነ ማንኛውም ወገን የዓለም መሪ ይሆናል" ማለታቸው ይታወሳል።

ሀገራት እያደረጉት ያለውን ፉክክር ስንመለከት የፕሬዚዳንቱ ንግግር ትክክል እንደነበር ታሪክ እያሳየን ይገኛል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በማበልጸግ ቻይና እና አሜሪካ መሪነቱን የጨበጡ ሲሆን ሌሎች ሀገራት በረጅም ርቀት ይከተሏቸዋል። በተለይም የቻይናው ዲፕሲክ (DeepSeek) ኩባንያ በፈረንጆቹ ጃንዋሪ ወር ያስተዋወቀው እና እጅግ ቀላል በሆነ መንገድ የሚሠራው ‘ኤአይ ሞዴል’ የዓለምን ትኩረት የሳበ ነበር።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ንቪዲያ (Nvidia) ለቻይና ቺፖችን እንዲሸጥ ፈቃድ በመስጠታቸውም ወቀሳ ደርሶባቸው ነበር።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ ጉዳዮች ወደ ኋላ መቅረቷ የጎዳት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በኤአይ (AI) ቴክኖሎጂም ወደ ኋላ መቅረት እንደሌለባትና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
ሌላው ባሳለፍነው የፈረንጆች 2025 ዓመት የዓለምን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ካገኙት ታላላቅ ክስተቶች መካከል የእስራኤል እና የኢራን የ12 ቀናት ጦርነት ተጠቃሽ ነው።
በዚህም በፈረንጆቹ ጁን 13 ቀን እስራኤል ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግላቸው የኢራን የኑክሌር ማዕከላት ላይ ‘ኦፕሬሽን አይረን ፊስት’ የተሰኘ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም ዘጠኝ የሚደርሱ የኢራንን ከፍተኛ የኑክሌር ሳይንቲስቶችን መግደሏን አስታወቀች።

ከዚህ ያልታሰበ የእስራኤል ጥቃት በኋላም ወትሮውንም ሰላም የራቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ወደለየለት የጦር ቀጠና ተቀየረ።
የኢራንን የአፀፋ ምላሽ በመስጋት በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰረዙ፤ አካባቢው ውጥረት ነግሦበት አያሌ አየር መንገዶች ለወትሮው የሚጠቀሙበትን የአየር ክልል በመተው ለከፍተኛ የነዳጅ ወጪ ተዳረጉ።
ይህ የእስራኤል ጥቃት ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላም በሳይንቲስቶቿ ግድያ ክፋኛ የተቆጣችው ቴህራን ከ150 በላይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ወደ ቴል አቪቭ እና ሐይፋ ከተሞች አስወነጨፈች። ይህ ጥቃት በእስራኤል ከተሞች ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮ ነበር።
ከቀናት በኋላም አሜሪካ ሰባት "ቢ-2 ስፒሪት" (B-2 Spirit) ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን በመጠቀም "ኦፕሬሽን ሚድናይት ሐመር" በተሰኘ ዘመቻ የኢራንን የከርሰ ምድር የኑክሌር ጣቢያዎች 30 ሺህ ፓውንድ ክብደት ባላቸው "ባንከር ባስተር" ቦምቦች መደብደቧን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

በምሽቱ በተላለፈው በዚህ የትራምፕ መግለጫ "ዛሬ ምሽት ለዓለም ደኅንነት ሲባል የአሜሪካ ጦር በኢራን የኑክሌር ማዕከል ላይ ጥቃት ሰንዝሯል" በማለት በተራራ ሥር የተገነባው የፎርዶው ኑክሌር ጣቢያ በግዙፎቹ “ቢ-2 ቦምበር” ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መመታቱን ተናገሩ።
በማግስቱ የአሜሪካን ጥቃት በመቃወም በቴህራን ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ። የኢራን ባለሥልጣናትም ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ከባድ አፀፋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናገሩ።
ይህንን ተከትሎም የዓለም የነዳጅ ገበያ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየት ጀመረ።
በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ነበር።
በዚህ መልኩ የተጀመረው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ለተከታታይ ቀናት ቀጥሎ፣ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የሚሳኤል ልውውጦች በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በወሰዱት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጣልቃ ገብነት በተደረገ የሁለትዮሽ የተኩስ አቁም ለ12 ቀናት የቆየው ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲቆም ተደረገ።
"የድሆች አባት" በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በሳምባ ምች ሕመም በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቫቲካን ያስታወቀችበት እና እርሳቸውን ተክተው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛው የካቶሊክ ርዕሰ ጳጳስ በመሆን የተሾሙት በዚህ ባገባደድነው የ2025 ዓመት ነበር።

ሌላው በ2025 በዓለማችን ታላቅ የዜና ሽፋን ተሰጥቷቸው ካለፉ ታላላቅ ሁነቶች መካከል የዓለም ሙቀት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩ ነበር።
በዚህ የዓለም የአየር ንብረት ቀውስ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የሙቀት መጠኑ ከ45 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ አንዳንድ ከተሞች ለቀናት እንቅስቃሴ እስከማቆም ደርሰው ነበር።
ይህ ሙቀት የፈረንሳይ የኑክሌር ማብላያ ጣቢያዎች እንዲቆሙ፣ የኤሌክትሪክ ዋጋ እንዲንር እና በ10 ቀናት ውስጥ የ2 ሺህ 300 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኖ አልፏል።

የፈረንጆቹ 2025 ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ክስተቶችም የተስተናገዱበት ሆኖ ወደ መቋጫው ደርሷል።
በዋሲሁን ተስፋዬ