በመደመር ዕሳቤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥና ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።
ብቁ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመፍጠር ዛሬ ላይ መሥራት ወሳኝ በመሆኑ፣ የለውጡ መንግሥት ንቁና ውጤታማ ትውልድን ለማፍራት የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ማስጀመሩ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት በርካታ ተማሪዎች የትምህርት ገበታቸውን በንቃት በመከታተል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት ጤና እና ሥርዓተ ምግብ ባለሙያ የሆኑት አቶ አበበ ጥላሁን፤ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር መጀመሩ ብቁ ትውልድ ለመፍጠር ከማገዙ ባለፈ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መቅረፍ ማስቻሉን ይገልጻሉ።
አቶ አበበ ጥላሁን ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ቀደም ሲል ተማሪዎች በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ለሕመም እና ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጡ እንደነበር፣ ይህም ከትምህርት ገበታቸው እንዲስተጓጎሉ ያደርጋቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
የምገባ መርሐ ግብሩ ለበርካታ እናቶች ትልቅ እፎይታ መስጠቱን የጠቀሱት ባለሙያው፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ8 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ይህም ተማሪዎች በንቃትና በውጤታማነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን አክለዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ እስከ እ.ኤ.አ 2030 ድረስ ሁሉንም የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ተሰንቆ እየተሠራ ይገኛል።
በሜሮን ንብረት