Search

የሦስቱ መርከበኞች የማይረሳ የቀይ ባሕር ታሪክ

ሰኞ ጥር 04, 2018 903

የባሕር ሃይል ሕይወት ተዝቆ የማያልቅ ትዝታ እና ገጠመኝ አለው፤ እያንዳንዳቸው መርከበኞች ልምድ እና ትዝታቸውን ቢጠየቁ አወግተው የማይጨርሱት መፅሐፍ የሚሻገር የሚነገር እና የሚፃፍ ታሪክ አላቸው።

በቀድሞ የኢትዮጵያ የባሕር ሃይል ውስጥ በ1964 የኢትዮጵያ የባህር ሃይል አባል ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ ለ20 ዓመታት አገልግለዋል ሌተናል ፈረደ አየለ።

ከዓመታት የአገልግሎት ዘመን በኋላ ከአሰብ 60 ኪ.ሜ የባሕር ጠረፍ ባራሶሊ የተባለ ቦታ የኢትዮጵያ መርከብ ባልታወቀ ምክንት በመቆሟ ጉዳዩን እንዲያጣሩ ከአዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት ትዕዛዛ መጣ።

እናም መርከቧ መሬቱን ተጠግታ ቆሟ ይሆን ወይስ በአደጋ ምክንያት አሊያም  በብልሽት  መቆሟን ለማረጋገጥ ሦስት መርከበኞች ተመደቡ።

በትዕዛዙ መሰረት ሌተናል ፈረደ አየለ፣ በወቅቱ የአጠቃላይ የባህር ሃይል የዘመቻ መኮንን የነበሩት ኮሞዶር ጌታቸው ስዩም  እና አንድ ጥልቅ ዋናተኛ በመሆን ጠረፍ ላይ ወደ ቆመችው መርከብ አቀኑ፡፡

በትልቋ ጦር መርከብ ኢትዮጵያ የሬድዮ ማናጀር የነበሩት ሌተናል ፈረደ አየለ ከአስር ኪ.ግ የማያንስ መጠን ያለውን ሬድዮ ተሸክመው ከትልቋ ጦር መርከብ ኢትዮጵያ በትንሽ ጀልባ በመውረድ ሶስት ሆነው ወደ ቆመችው መርከብ ጉዞ ጀመሩ።

እንደ ትናትና አደጋ አጋጥሟት የቆመችው መርከብ በውስጧ የነበሩትን ሰዎች ቀደም ተብሎ ወደ ሌላ መርከብ የምዘዋወር ሥራ ተሰርቷል።

ከጀልባው እስከ ቆመችው መርከቧ ያለው ርቀት እምብዛም ቢሆንም መርከቧ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመመርመር ምሽት በመሆኑ እሰኪነጋ ለመጠበቅ ሥስቱ መርከበኞች በቅርብ ርቀት ለማደር ተሰነዳድተዋል፡፡

ከለሊቱ አስር ሰዓት ገደማ ይሆናል አከባቢው በፍንዳታ ድምፅ ሲጥለቀለቅ፤ መርከቧ ላይ ጉዳት እንደደረሰ መረጃ የደረሳቸው ሽፍቶች መርከቧን በቦንብ አፈነዷት።

ከሶስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ቆመው በአጉሊ መነፅር መርከቧን ይመለከቱ የነበሩት ሶስቱ ለተልዕኮ የመጡት መርከበኞች ወደ መርከቧ በጀልባ ጉዞ ጀመሩ።

ለመድረስ ሀምሳ ሜትር ያህል ርቀት ሲቀራቸው ከፍተኛ የሩምታ ተኩስ ከተለያየ አቅጣጫ ይዘንብባቸው ጀመር።

በየብስ ላይ ሆኖ የእነርሱን እንቅስቃሴ ሲከታተል ከነበረው የሽፍታ ቡድን የተከፈተባቸውን ተኩስ በፍፁም የልጠበቁት በመሆኑ በድጋጤ ጀልባዋን እናዞራለን ብለው በፍጥነት ሲሞክሩ ጀልባዋ ተገልብጣ እነሱ ከስር ጀልባዋ ደግሞ ከላይ ሆነች።

በአጋጣሚ ክስተት ወደ ባሕር የገቡት ሦስቱ መርከበኞች ከሚተኮሰው ጥይት ለማምለጥ ወደ ውስጥ መስረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ሆነ።

ከሬድዮ ማናጀሩ ወገብ ላይ ከታሰረው ሬዲዮ በተጨማሪ ኡዚ የሚባል መሳሪያ በአንድ እጁ ይዞ በሌላኛው እጅ ደግሞ ባለ ገመድ የሬድዮ መነጋገሪያ ተሸክሞ በደርቅ ለሊት በድቅድቅ ጨለማ ከሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚዘንበውን የጥይት ሩምታ ለማምለጥ ከባህር ጋር ግብ ግብ ገጥመዋል፡፡

የባህሩ ውሃ ቅዝቃዜ እና ጨዋማነት፣ ከላይ የጥይት ሩምታ እንዲሁም ለመተንፈስ ካለው ጭንቀት ጋር ተዳምሮ ለመዋኘት እጅግ አዳጋች ሆኗል።

የባህር ጠላቂው እና ኮሞዶር ጌታቸው ስዩም በእጃቸው ምንም ባለመያዛቸው መዋኘት እንዲችሉ አድርጓቸዋል።

በዚህ ጉዞ ውስጥ ጀልባዋም እንደተገለበጠች ወደ ተቃጠለችው መርከብ በመጠጋት ከለላ ለማግኘት በመሞከር ላይ ናቸው።

ሌተናል ፈረደ አየለ ግን የያዟቸው ዕቃዎች ክብደት እንደፈለጉ ለመዋኘት ስላላስቻላቸው ወደ ውስጥ መስረግ ጀምረዋል፡፡

ሌተናል ፈረደ አየለ “ሁሉንም ይዞ መጓዝ እና በሕይወት መቆየት የማይቻል በመሆኑ ኡዚውን ለመጣል ተገደድኩ” ይላሉ በወቅቱ በሕይወት ለመቆየት ያደርጉ የነበረውን ግብ ግብ ሲያስታውሱ።

ከትልቋ ጦር መርከብ ኢትዮጵያ ይዘዋቸው የመጡት መርከበኞች ጀልባዋ መገልበጧን እና እየተተኮሰባቸው እንደሆነ ሲያውቁ የመልስ ተኩስ ወደ ሽፍቶቹ ከፈቱ።

በሁለት አቅጣጫ ከሚመጣው ጥይት ለማለጥ እና በውሃ ውስጥ ሕይወቱን ለማቆየት የሚታገለው የያኔው ሌተናል ፈረደ ወደ ባሕሩ በመስመጥ ለሕይወቱ መታገል አማራጭ የሌለው መንገድ ነበር።

ሁለቱ መርከበኞች በቦንብ ፈንድታው በመንደድ ላይ ወዳለችው መርከብ ከለላ በማድረግ ሽፋን አገኙ ሌተናሉ ግን እርዳታ እና አየር ለማግኘት ከሚተኮሰውም ጥይት ለማምለጥ ብቅ ጥልቅ እያለ ከ20 ደቂቃ በላይ በባሕሩ ውስጥ ለመቆየት ተገደደ፡፡

የባህሩን ጨዋማ ውሃ አልፎ አልፎ አየር ለማግኘት በመጠጣቱ ምክንያት ሆዱ መነፋት ጀምሯል፤ በተሸከማቸው እቃዎች ምክንያት ሰውነቱ እየዛለ መዋኘት እየተሳነው ነው፡፡

ከመርከቧ ትልልቅ መሳሪያዎች እየተተኮሰባቸው ፋታ በማጣታቸው ሽፍታዎቹ መሸሽ ሲጀምሩ ሌላ የእርዳታ ጀልባ ከመርከቧ መጥቶ ላይፍ ሪንግ የምትባል መሳሪያ ቢወረውሩለትም እርሱን ይዞ በጀልባዋ ፍጥነት መጓዝ ባለመቻሉ ውሀ ውስጥ መስመጥ ጀመረ፡፡

ሌላ ጠላቂ ዋናተኛ መጥቶ አካባቢው ላይ ዳሰሳ በማድረግ ሞቷል ብለው ይዘውት ሲሄዱ አይኑ ፈጦ ባይርገበገብም እንደፈጠጠ ባይከደንም ትንፋሹ ግን አልተቋረጠም ነበር፡፡

እስከ አንድ ሳምንት በምፅዋ ሆስፒታል ውስጥ እራሱን እንደሳተ ቆየ፤ ከሳምንት ራስን መሳት በኋላ ግን መንቃት ችሎ ዳግም በመርከበኝነት ሀገሩን ማገልገል ችሏል፡፡

የባሕርተኞች ሕይወት መስመሩ ብዙ አስተምህሮቶ ጥልቅ ሆኖ የምናገኘው እዚህ ላይ ነው። ብዙ መስዋዕትነትን መቀበል ከአስቸጋሪው ፈተና በኋላ እንደገና ሀገርን ማገልገል የሀገር ሰንደቅን በህሊናም በመርከባቸውም ላይ ተሸክመው መጓዝ።

የዛሬው ሌተናል ፈረደ ታዲያ ያኔ ያሳለፉትን ጊዜ ሲያስታውሱት ብዙ ታሪኮች ተከውነው ውድ የሰው ልጅ ሕይወት ተከፍሎ የተጠበቀ ባሕር ሃይል ባለቤት መሆናቸው ቀዳሚው ነው። በመስዋዕትነት የተጠበቀው ባሕር ሃይል እንደዋዛ መፍረሱ የሕይወት ዘመን ቁጭታቸው ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ሃይል በነበረበት ወቅት ለኢትዮጵያ ጉልህ ድርሻ ሲያበረክት የቆየ መሆኑን ተናግረው የማይጠግቡት ሌተናል ፈረደ የባሕር ሃይል የአንድነት እና የጋራ ሥራ ውጤት መሆኑን አይዘነጉትም። እዚህ ላይ ታዲያ የሀገር ፍቅር ሲጨመርበት ባሕር ሃይል ሁሉ ነገር ይሆናል።

 

 

በንፍታሌም እንግዳወርቅ