በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ’ገበታ ለትውልድ’ ውጥን አካል የሆነው ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’፤ ማህበረሰብን ለማበልጸግና ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የባለራዕይ መሪ የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ምስክር ነው።
ሎጁ በተለያዩ የፍራፍሬ እና የደን ዛፎች በለመለመ 78,000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ተፈጥሯዊ የ"ሰማያዊ ዓይን" ፍልውሃ መዋኛ ፣ ሁለት ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቆች እና 3.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግር ጉዞ (ሀይኪንግ) ምቹ መንገድ አካቷል።
የማረፊያ ክፍሎቹንም በተመለከተ፦ የግል መዋኛ ገንዳ ያላቸው ሁለት ፕሬዝዳንታዊ ቪላዎች፣ አስራ ሁለት እርስ በእርስ የተያያዙ የመኝታ ክፍሎች እና አስራ ስድስት ባለ አንድ መኝታ ቤቶችን ይዟል።
በተጨማሪም ዘመናዊ የምግብ አዳራሾች፣ የእንግዳ መቀበያ ህንፃ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የቢሮ ክፍሎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና ሁለት ሄሊኮፕተሮችን በአንድ ጊዜ ማሳረፍ የሚችል ስፍራ (ሄሊፓድ) ያካተቱ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል።
ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ከቱሪስት መዳረሻነቱ ባለፈ፣ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን በመሳብ ታላላቅ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ተደማሪ ዐቅም ነው።
በመስተንግዶ እና በአገልግሎት ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአካባቢው ኢኮኖሚ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ሲሆን ፕሮጀክቱ በጠንካራ አመራር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻን የማቅረብ የገበታ ለትውልድ መርሃ-ግብር ርዕይን ሰንቆ ቀጣይነት ላለው ቀጣናዊ ዕድገት እንደ ወሳኝ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።