Search

ወድቀህ ተነሣ እንደ መገጭ ግድብ፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 56

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ለዓመታት ተጓትተው የሀገር ሀብት ፈሶባቸው መክነውና ባክነው የቀሩ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ከሞት እያስነሱ ማፋጠን የብልጽግና መንግሥት ልዩ መለያ መሆኑን ገለጹ።
የግንባታ ሂደቱን የተመለከቱበትን የመገጭ የመጠጥ ውኃ ግድብን እንደ አስረጅ ምስክር የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት እሱ ራሱ የጀመራቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ተጀምረው የውልደት ስብራት የገጠማቸውን ፕሮጀክቶች አዲስ እስትንፋስ በመስጠት ግንባታቸውን እያፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጎንደርን የውኃ ጥም ይቆርጣል፣ የገበሬውን መሬት ያጠጣል እንዲሁም የአካባቢውን ምኅዳር ይለውጣል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ግድብ አሁን ላይ በደረሰበት አስደሳች ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቀደም ሲል በአካባቢው ሰው ዘንድ "አቁሞ ያስቀርህ እንደ መገጭ ግድብ" ተብሎ ይነገር የነበረው አሉታዊ ተረት መቅረቱን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ አሁን ግን የመንግሥት ቁርጠኝነት ብሂል አስቀይሮ ሕዝቡ "ወድቀህ ተነሣ እንደ መገጭ ግድብ" ብሎ መተረት መጀመሩን በአድናቆት ገልጸዋል።