ያኔ በዚያ ጊዜ ሁለቱም ክለቦች እንደ አሁኑ ከዋንጫ ጋር ሳይጣሉ ብቻቸውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋና ምልክት በሆኑበት 1990ዎቹ መጨረሻ እና 2000ዎቹ መጀመርያ እርስ በእርስ የሚያርጉት ጨዋታ ላይ ሌላ ቅመም የሚጨምሩበት ተጫዋቾች ነበሩ፡፡
የአየርላንድ ሪፐብሊኩ አማካይ ሮይ ኪን እና ፈረንሳዊው አማካይ ፓትሪክ ቬራ፡፡
ዓለም ላይ የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆኑት ማንችስተር ዩናትድ እና አርሰናል የሚገናኙበትን ጨዋታ ይበልጥ እዲጠበቅ የሚያደርገው ምክንያት ብዙ ነው::
አሸነፈ ተሸነፈ ከሚለው ውጤት ያለፈ የሁለቱ ጀብደኞች ትንቅንቅ ከጨዋታው እኩል ብዙ ተብሎለታል፡፡
ዩናይትድ ከአርሰናል በሚገናኙበት ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ከሚደረገው የደጋፊዎች ብሽሽቅ ሜዳ ላይ ቴአትር እስከሚመስለው የተጫዋቾች ትንቅንቅ ውስጥ ኪን እና ቬራ ዋና ተዋንያን ሆነው ዓመታትት አሳልፈዋል፡፡
በሀይብሪም ይሁን በኦልድ ትራፎርድ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች ለበርካታ ጊዜ ግጭት ውስጥ ቢገቡም የኪን እና ቬራን ያክል ግን ነገሩን ሌላ መልክ የሚያሲይዝ አይደለም፡፡
የሁለቱ አማካዮች ግጭት የሚጀምረው ከሜዳ ውጭ ነው፡፡ 2005 ላይ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታው በሀይብሪ ከመጀመሩ በፊት ገና ከመልባሻ ክፍል በሚወጡበት ሰዓት ለጸብ የተጋበዙበት አጋጠሚ እና የእለቱ ዋና ዳኛ ግርሀም ፖል ተጫዋቾቹን ለማረጋጋት ስራቸውን ከሜዳ ውጭ የጀመሩበት አሁንም ድርስ እንደ አዲስ የሚታወስ ነው፡፡
ሁለቱም ተጫዋቾች የቡድኖቻቸው አምበል መሆናቸው እና ከምንም በላይ ደግሞ የሚጫወቱበት ቦታ ተመሳሳይ መሆኑ በእያንዳንዱ ሁነት ይበልጥ እንዲገናኙ አድርጓቸዋል፡፡
ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ የሚጠቀሙት ጉልበት፣ የሚሰሩት ጥፋት በተለይ እርስ በእርስ አንድ ለአንድ ከኳስ ጋር ሲገናኙ እነሱን ማየት የማያዝናናው የለም፡፡
ኳሱን ከመጫዎት ይልቅ አንደኛው የአንደኛውን ዕግር ለመስበር ወይም ጥፋት ለመስራት የሚጓዙበት ርቀት ለዓመታት የክለቦቻቸው ምልክት ሆነው እንዲያሳልፉም አድርጓቸዋል፡፡
የቡድኖቻቸው አምበል መሆናቸው ሜዳ ውስጥ የሚፈጠሩ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር እድል የሚሰጣቸው ቢሆንም እነሱ ግን የዳኞች ፈተና ሆነው ለገላጋይ አስቸጋሪ የሆኑባቸው አጋጣሚዎች ቀላል አይደሉም፡፡
ከአርሰን ቬንገር ጋር እኩል ሀይብሪ የደረሰው ፓትሪክ ቬራ በክለቡ በቆየባቸው 9 ዓመታት አርሰናል ለትልልቅ ክብሮች እንዲፋለም በማድረግ እና በተለይ ከዩናትድ ጋር ያለው የተቀናቃኝነት ደረጃ ከፍ እንዲል በማድረግ ትልቁን የቤት ሥራ ሰርቷል፡፡
በቀይሰይጣናቱ ቤት 13 ዓመታትን ያሳለፈው ሮይ ኪንም የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቡድን አስፈሪ ሆኖ ለዓመታት እንዲዘልቅ ካደረጉ ተጫዋቾች ቀዳሚው ነው፡፡
በቦክሱ ዓለም አሜሪካውያኑ ጆ ፍሬዘር እና ሙሀመድ አሊ ያደረጉትን የምንጊዜም ትልቅ የቦክስ ፍልሚያ ያክል የሁለቱ ተጫዋቾችም ትንቅንቅ በዚያ ልክ የሚነሳ ነው::
ፓትሪክ ቬራ በአሁኑ ሰዓት የጀኖዋ አሰልጣኘ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡ አሰልጣኝነት አልሳካልህ ያለው ሮይ ኪን ደግሞ በእግር ኳስ ተንታኝነት እየሰራ ነው፡፡
የማንችስተር ዩናትድ እና የአርሰናል የተፎካካሪነት መገለጫ ሆነው ከተሳሉት ሁለቱ ከዋክብት በኋላ ሁለቱ ቡድኖች የሚገናኙበት ጨዋታ በዚያ ልክ ትልቅ ፉክክር የሚደረግበት ባይሆንም አሁንም የሚጠበቅ መርሀ ግብር ነው፡፡
በአዲሱ የውድድር ዓመት በመጭው እሁድ ኦልድ ትራፎርድ ላይ ማንችስተር ዩናትድ ከአርሰናል የሚገናኙ ይሆናል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ