ከ75 ዓመታት በላይ አፍሪካን ከዓለም ያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጠቀምበት የቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅሙ በዓመት እስከ 25 ሚሊዮን የደረሰ ቢሆንም፤ እያደገ ያለውን የአቪየሽን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም።
ይህን ፍላጎት ለማሟላትም ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፤ በ10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያን ለመንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
አዲሱን የአውሮፕላን ማረፊያ መገንባት እያደገ ያለውን የአቪዬሽን ዘርፍ ፍላጎት ለሟሟላት፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና ሀገሪቱ በአቪየሽን ዘርፍ መሪነቷን አጠናክራ እንድትቀጥል ያስችላል ብለዋል የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ።
ፕሮጀክቱ የአውሮፕላን ማረፊያ ብቻ ሳይሆን፣ የፓና አፍሪካ ትስስርን ለማጠናከር፣ ለኢኮኖሚ ፣ለቱሪዝም እና ለንግድ እድገት እንዲሁም ለባህል ልውውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው የመንገደኞች እና የካርጎ አገልግሎት በመስጠት፤ አብረው መስራት የሚፈልጉ የንግድ አጋሮችንና ዓለም አቀፍ አልሚዎችን መሳብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
አፍሪካን ከዓለም፤ ዓለምን ከአፍሪካ ለማገናኘት፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የቱሪዝም ፍሰት በእጥፍ ለማሳደግ እና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ገንቢ ሚና ያበረክታልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የሰዎችንና የሸቀጦች ነፃና አስተማማኝ ዝውውር በማረጋገጥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን ለማስተሳሰርም ያግዛልም ብለዋል።
ዘመናዊ የካርጎ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የሚገነባው የቢሸፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማጓጓዝ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ከአራት እጥፍ በላይ በማሳደግ፤ በዓመት ከ110 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማስናገድ ያስችላልም ነው የተባለው።
ፕሮጀክቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ከማስቻሉም በላይ፤ በአከባቢውም ሆነ በአከባቢው ማኅበረሰብ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትልም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ከሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አጀንዳዎች ጋር የተጣጣመ ነው ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የግል ዘርፉን ለማበረታታት፣ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብና የሀገሪቱን የሎጂስቲክስ አቅም ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚገነባው የቢሸፍቱ ዓለምአቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፥ በ3975 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፤ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖራት ያስችላል።
ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ 80% በመቶ በራሱ እና ብድር በማፈላለግ የሚሸፈን ሲሆን 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ባንኩ ፋይናንስ ለማድረግ ትላንት ስምምነት ፈርሟል፤ 20% በመቶ ወጪ በአየር መንገዱ የሚሸፈን ይሆናል።
በላሉ ኢታላ