የዓሣና ውኃ ሀብትን ለማሳደግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት አባል ሀገራት (ኢጋድ) በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኢጋድ አባል ሀገራት የተሳተፉበት የዓሳና ውኃ ሀብትን ለማሳደግ ያለመ መድረክ በአዲስአበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ወክለው ንግግር ያደረጉት የኢጋድ የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ዲቪዥን ዳይሬክተር ዳህር ኤልሚ (ዶ/ር)፤ በቀጣናው ዘላቂ የሆነ የዓሣ ሀብት ልማትና አስተዳደር የጋራ ትብብርን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ቀጣናው የዓሣ ሀብት በስፋት የሚገኝበትና ለምግብ ዋስት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና የውጪ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ሰፊ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ በመድረኩ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በዘርፉ በማይስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ሀገራት በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም ተብሏል።
በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የዓሳ ሀብቷን ምርታማነት እያሳደገች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ በቀጠናው ያለውን የዓሳ ሀብት አያያዝና ምርታማነት ለማሳደግ በቅንጅት ትሰራለች ብለዋል።
በአባዲ ወይናይ