ዓለም ዓቀፉ የወጣቶች ቀን "የተደመረ የወጣቶች አቅም ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት" በሚል መሪ ቃል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በክልሉ የርዕሰ መስተዳድሩ የማሕበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ በዚሁ ወቅት፥ ወጣቶች እና የበጎ ፍቃድ ተግባራት የማይነጣጠሉ በመሆናቸው የዘንዱሮው የወጣቶች ቀን በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ይከበራል ብለዋል።
ወጣቶች በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፈጠራ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ድንቅነሽ ማሞ በበኩላቸው፥ በዓሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ ይከበራል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ በወጣቶች መካከል የልምድ ልውውጥ ከመደረጉ በተጨማሪ ለአረጋውያን የማዕድ ማጋራት ተከናውኗል።
የዘንድሮው የወጣቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
በነስረዲን ሀሚድ
#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #የወጣቶችቀን #በጎፈቃድ