በመንግስትና በማኅበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችንና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን፤ ከ23.3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማዳን እንደተቻለ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ የተባለው እየተካሄደ በሚገኘው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሴክተር አራተኛ ጉባዔ ላይ ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክረምትና የበጋ ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ25ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ነው የገለጸው።
በዚሁ ወቅት የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርትን ያቀረቡት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ማዕረግ መኮንን፥ በክረምት እና የበጋ ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብሮች "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል መካሄዱን ጠቅሰዋል።
በተለያዩ የስምሪት መስኮች 25.9 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ ችለዋልም ነው ያሉት።
ከ59.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሕበረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፥ ለዜጎች የላቀ ክብር በትጋት እንሰራለን ያሉ ሲሆን፤ በተለይም ተቋሙ የጀመረውን የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ዝርጋታን በማጠናከር ዜጎችን በልማት ተሳታፊ ለማድረግ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በአዲሱ ገረመው