ፍትሐዊነት ያለው የገቢ አሰባሰብን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን እየተከተለ መሆኑን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው እያከናወነ ባለው የሪፎርም ሥራ የደረሰኝ ቁጥጥርን ከሌብነት የፀዳ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን የቢሮው ኃላፊ ቢኒያም ምክሩ ተናግረዋል።
በግብር አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚፈጠር ብልሹ አሰራርን ለመፍታት 'ኪው አር ኮድ' የታተመበት ዲጂታል መታወቂያ ለቁጥጥር ባለሙያዎች መሰጠቱን ኃላፊው አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም የመስሪያ ቤቱ ተቆጣጣሪ በመምሰል በነጋዴው ማህበረሰብ ላይ የማጭበበር ወንጀል ይፈፀም እንደነበር አንስተው፤ ግልፅነት ያለው የገቢ አሰባሰብ እንዲኖር ቴክኖሎጂው ያግዛል ነው ያሉት።
ቢሮው ዛሬ ያስተዋወቀው ቴክኖሎጂ፤ ማንኛውም ነጋዴ በቀላሉ በእጅ ስልኩ በመጠቀም በቁጥጥር ባለሙያው መታወቂያ ላይ ያለውን የ'ኪው አር ኮድ' ስካን በማድረግ ብቻ ባለሙያው መስሪያ ቤቱ የወከለው መሆን እና አለመሆኑን ለመለየት እንደሚያስችለው ተነግሯል።
በተጨማሪም የቢሮው የቁጥጥር ባለሙያዎች ተመሳሳይ ዩኒፎም እንደተዘጋጀላቸው ተጠቁሟል።
ቴክኖሎጂው ከዚህ ቀደም በግብር ከፋዩ ላይ በተደጋጋሚ ያጋጥም የነበረውን መጭበርበር ለመከላከል ትልቅ ሚናን ይጫወታልም ተብሏል።
ቢሮው በግብር አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ማነቆ ፈጥረዋል ያላቸውን ተግዳሮቶች በመለየት የእርምት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
በሳምሶን ገድሉ