Search

ለስደት ተመላሾች የሚሰጠው የሥነ-ልቦና እና ማኀበራዊ አገልግሎት

Aug 12, 2025

መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው የሚመለሱ  ዜጎች አስፈላጊውን የሥነ-ልቦና እና የማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ሲል የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሴክተር አራተኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት በሰጠው ማብራሪያ፤ ሕፃናትን ጨምሮ ከ95 ሺህ በላይ ዜጎች ከተለያዩ ሀገራት ወደኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡

ከተመላሾቹ መካከል ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች ናቸው፡፡

በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማዕረግ መኮንን እንደገለጹት፤ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከየመን ከቤይሩት እና ከኦማን የተመለሱ ዜጎች አስፈላጊውን የሥነ-ልቦና እና የማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው እና ከማኀበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

 

በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሞክሩ በድንበር አካባቢ ለተያዙ ዜጎች በሙሉ የሥነ-ልቦና እና ማኀበራዊ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

በዚህም በሞያሌ፣ በጋላፊ፣ በመተማ፣ በቶጎጫሌ ኬላዎች ተይዘው የተመለሱ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች ተገቢውን የሥነ-ልቦና እና ማኀበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ መደረጉንም አቶ ማዕረግ ጠቅሰዋል፡

በተጨማሪም ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 151 ተመላሾች ነፃ የሕክምና አገልግሎት፣ የኢኮኖሚ መልሶ ማቋቋም እና የመጠለያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ከዚህም ባሻገር በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በገጠር እና በከተማ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ 1.2 ሚሊየን ዜጎች ወቅቱን የጠበቀ ወርሀዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉም ተገልጿል።

 

 በአዲሱ ገረመው