Search

ክረምት እና የአለባበስ ስርዓታችን

Aug 13, 2025

አሁን ላይ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ የአየር ጠባይ መረጃን በስማርት ስልካችን ላይ በቀላሉ ልንከታተለው የምንችለው ጉዳይ ሆኗል፡፡

ኢቢሲም ለዘመናት ከዜና እወጃው እኩል የአየር ጠባይ መረጃዎችን ከኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን ሲያቀርብ ኖሯል፡፡

መረጃውን ምን ያህል ግለሰቦችና ተቋማት እንደተጠቀሙበት የራሱን ጥናት ቢፈልግም የአየር ጠባይን አስመልከቶ የሚሰሩ ዕለታዊና ወቅታዊ መረጃዎች መቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡

ስማርት ስልካችን ላይ የሚጫኑ የአየር ጠባይ መከታተያ መተግበሪያዎች የየዕለቱን እንዲሁም የመጪዎቹን ጥቂት ቀናት የአየር ሁኔታ ትንበያ ጭምር የሚያስቀምጡ በመሆናቸው አሁን ላይ መረጃው እጃችን ላይ ነው፡፡  

ፕሮቶኮል ዝግጁነት ሲሆን፤ ቀድሞ ለሁኔታዎች መዘጋጀት ደግሞ የዘመናዊነት መገለጫ ተድርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ 

የፕሮቶኮል ጉዳይ አማካሪና አሰልጣኝ እንዲሁም የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው አቶ አበበ ሙሉ፤ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ስናስብ የሜቲዎሮሎጂ መረጃን በማየት እንደ ወቅቱ የአየር ጠባይ የአለባበስ ሁኔታችንን ለመወሰን እንደ አንድ የመዘጋጃ መስፈርት ብናካትተው የተሻለ ቀን እንዲኖረን ያግዛል ይላል፡፡

የሜቲዎሮሎጂ መረጃ የአየር ጠባይ አለባበሳችንን፣ በሰዓት መገኘት አለመገኘታችንን፣ የኩነት እቅዳችንን እንዲሁም የእንግዶቻችንን ምቾት ጭምር የሚወስን በመሆኑ በጣም ጠቃሚ መረጃ ነው ሲለም ይገልጻል፡፡

ከቤት ከመውጣታችን በፊት መስታወት ብቻ ሳይሆን ሰማዩንም ማየት ይገባል የሚለው የፕሮቶኮል ባለሙያው አቶ አበበ፤ አሁን ላይ ደግሞ ሰማዩ እጃችን ላይ ሆኗል፤ በእጅ ስልካችን ላይ ሁሉንም መመልከት እንችላለን ሲል ይጠቅሳል፡፡

ሜቲዎሮሎጂ አሁን ላይ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን የየዕለት እንቅስቃሴን የሚወስን በመሆኑ ከሚያስፈልጉ ጠቃሚ መረጃዎች አንዱ እንደሆነ ይገለጻል፡፡

የሰዎች ስሜትና ጠባይ እንዲሁም ባህሪ የገጽታቸው አንድ አካል ነው የሚለው የፕሮቶኮል ባለሙያው፤ አየሩ አለባበሳችን ላይ ብቻ ሳይሆን ስሜታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ከሆነ ይህንኑ መገንዘብና ቦታ መስጠት ተገቢ ነው ሲል ይናገራል፡፡

አለባበስ ባህልን፣ የተሰማራንበትን የስራ መስክና ኢንዱስትሪ መነሻ ያደርጋል የሚለው አቶ አበበ፤ ለአለባበስ ሌላው መነሻ ደግሞ የአየር ንብረትና የአየር ጠባይ ሁኔታ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

በተጨማሪም የደንብ ልብስ የተቀመጠ ሲሆንና የደንብ ልብስ ሳይኖር ነገር ግን ለዘርፉ የሚመጥን ገጽታችንን የሚያጎላ አለባበስ መከተል ለራሳችን እንዲሁም ለሌሎች በተለይም ለደንበኞቻችንና ለአጋሮቻችን የሰጠነውን ክብር የምናሳይበት መንገድ ነው ሲልም ይገልፃል፡፡

በአለባበስ ሌሎችን እናከብራለን፣ ለራሳችን የሰጠነውንም ቦታ እናሳይበታለን የሚለው አቶ አበበ፤ አለባበስ ምን ያህል ለነገሮች ትኩረት እንደምንሰጥ ማሳያ ተድርጎ እንደሚወሰድም ያነሳል፡፡

አንድን ሰው አለባበሱን አይታችሁ በምን ዘርፍ እንደተሰማራ ወይም ደግሞ በአለባበሱ መነሻ ብቻ ገምግማችሁ የሆነ ቦታ አስቀምጣችሁት አታውቁም?

ይህንን ብታደርጉ አይፈረድም ምክንያቱም አዕምሯችን ነገሮችን ገምግሞ አንድ ቦታ ማስቀመጥ ስራው ነው፡፡

ብዙ ጥናቶች ሰዎች በሁለት ሰከንድ ውስጥ ስለ አንድ ሰው ከገጽታው ወይም ከአለባበሱ በመነሳት ብቻ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርሱ ያስቀምጣሉ፡፡

የፕሮቶኮል ባለሙያው አቶ አበበ፤ አለባበሳችን ወይም ገጽታችን በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ከአየር ጠባዩ ጋር የተስማማ እንዲሁም ያለንበትን ዘርፍና የስራ ደረጃ የሚመጥን አለባበስ ኖሮን ማሳለፍ እንድንችል ተከታዮቹን ምክረ ሀሳቦች ያነሳል፡፡

የመጀመሪያው ከወቅቱ ጋር የሚሄድና የአየር ጠባዩን ከግምት ያስገባ የልብስ ዝርዝር ማዘጋጀት ነው የሚለው አቶ አበበ፤ ለወንዶች መለስተኛ ካፖርት በሽሚዝ እና ከረባት ላይ መደረብ በቂ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ይናገራል፡፡

ለሴቶችም እንዲሁ ሞቅ የሚያደርጉ የአንገት ስካርፎችን ጨምሮ ከወቅቱ ጋር የሚሄድ ካፖርት ወይም ሹራብ ደረብ ማድረግ ይመከራል ሲል ባለሙያው ምክረ ሀሳቡን ያክላል፡፡

ይህ በመደበኛ የስራ መስኮች ሲሆን ለሰራተኞቻቸው የደንብ ልብስ ያዘጋጁ ተቋማት ደግሞ መለያቸው የታተመበት ሹራብ ወይም ወፍራም ጃኬት ሊኖራቸው እንደሚችል ያነሳል፡፡

ኢትዮጵያ አስራ ሶስት ወር ሙሉ ፀሀይ የምታገኝ ሀገር መሆኗን የሚገልጸው አቶ አበበ፤ ክረምት እና በጋውን ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት እንዳለን አገራችንን ለማስተዋወቅ የዋለ የዘመናት መለያችን ሆኖ አገልግሎናል ሲል ተናግሯል፡፡

የአገራችን ትልቁ ጸጋ ሁሉም ወራት በሚባል ደረጃ የተለየ የአለባበስ ሁኔታ ሳይጠይቅ የምናሳልፈው በመሆኑ ትልቁ መታደል ነው ሲልም አክሏል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #outfit