የ1 ዓመት ከ8 ወር ዕድሜ ያለውን ህፃን በማገት 2 ሚሊዮን ብር የጠየቁ እና በወንጀሉ ተባብረዋል የተባሉ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
ወንጀሉ የተፈፀመው ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 1፡40 ገደማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አፍሪካ ህብረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልፀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ፋኑኤል ብርሃነ የተባለን የ1 ዓመት ከ8 ወር ዕድሜ ያለውን ህፃን ከመኖሪያ ቤቱ በስውር በመውሰድ ወደ ወላጅ አባቱ ስልክ ደውለው ህፃኑን እንዳገቱት ይገልፁላቸዋል።
ህፃኑን ለማስለቀቅም 2 ሚሊዮን ብር በአካውንት ገቢ እንዲያደርጉ በመጠየቅ በበህፃኑ ወላጅ አባት እና በቤተሰብ ላይ ጭንቀትና ድንጋጤን መፍጠራቸውን ኮማንደር ማርቆስ አብራርተዋል።
አቶ ብርሃነ ገ/ፃዲቅ የተባሉት የህፃኑ ወላጅ አባትም ስለ ሁኔታው በአቅራቢያቸው ለሚገኝ ፖሊስ በወቅቱ አሳውቀዋል።
ይህን ተከትሎ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የቄራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባደረገው ርብርብም ካህሳይ ተክላይ የተባለውን እና ከህፃኑ ወላጅ አባት ጋር ዝምድና ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልፀዋል።
የወንጀሉ ዋና አቀነባባሪ ነው በሚል ተጠርጥሮ በተያዘው ካህሳይ ተክላይ ላይ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ሥራ በወንጀሉ የተባበሩትን ፊሊሞን ገ/ማርያም፣ ተክሊት ህሉፍ እና ምህረት ዕድሉ የተባሉ ተጨማሪ 3 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉ በተፈፀመ በማግስቱ ሳሪስ አካባቢ በሚገኝ ሆቴል አልጋ በመከራየት ህፃኑን ይዘው ከተሸሸጉበት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።
በወንጀሉ የተጠረጠሩት አራቱም ግለሰቦች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBC #EBCdotstream #AAP #suspects