ልጆችን እራሳችን በገዛነው ስልክ የተነሳ እያጣናቸው በመሆኑ መፍትሔውን አውቆ መጠንቀቅ ይገባል ሲሉ የማኀበራዊ ጉዳዮች ባለሙያ እና የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት ደረጄ ግርማ ተናግረዋል።
ባለሙያው ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በልጆች ዕድገት ውስጥ አሉታዊ ተጽንኦ የሚያደርጉ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
ወላጆ በልጆች የሕይወት መንገድ ላይ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ያስታወሱት ባለሙያው፤ ወላጆች ከልጆቻቸው አካላዊ እድገት ባሻገር በመንፈሳዊ ፣ በማኀበራዊ፣ በስነልቦና ረገድ ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ ወላጆች የእራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
በቀደመው ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን የማይሆን ነገር እንዳይጀምሩ ቁጥጥር በማበጀት ከአላስፈላጊ ችግር ይታደጉዋቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ልጆች ስለጠየቁ ብቻ ለረጅም ሰዓታት የስልክ ስክሪን ላይ እንዲቆዩ ይደረጋል ብለዋል። ይህም ልጆቻችንን በገዛ ፈቃዳችን ለሚቆጣጠርብን ሌላ አካል እንደሰጠን ይቆጠራል ሲሉ አስረድተዋል።
ቴክኖሎጂ መጠቀም ጥሩ ቢሆንም ልጆች ያለ ልክ በመጠቀማቸው ስነልቦናዊ ጉዳት እንደሚደርስባቸውም አንስተዋል።
በማኀበራዊ ሚዲያ አሉታዊ አጠቃቀም ምክንያት ሲያድጉ እራሳቸውን የሚያጠፉ፣ ሱስ ውስጥ የገቡ፣ ለመጤ ባህል ተጋላጭ የሆኑ ልጆች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከመላክ እና ጥሩ ትምህርት ቤት ከማስማር ባሻገር በስልክ አጠቃቀማቸው ላይ ቁጥጥር በማድረግ ጥሩ ዜጋ የሚሆኑበትን መንገድም ማመቻቸት እነዳለባቸው አንስተዋል።
በአደጉት ሀገራት የሚገኙ ሕጻናትን ከአላስፈላጊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚከለክል አሰራሮች ወደ ሀገራችንም ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ ያሉት ባለሙያው፤ ወላጆች ከምንም ነገር ቅድሚ ለልጆቻቸው የአዕምሮ ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ሲሉም ነው የተናገሩት።
በሜሮን ንብረት