የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ግምታቸው ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ ሕገ ወጥ መድኃኒቶች እንዲወገዱ ማድረጉን አስታወቀ።
ሕገ ወጥ መድኃኒቶቹ በዋናነት የባለስልጣን መስርያ ቤቱን መስፈርት የማያሟሉ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ለአብነትም የወባን ጨምሮ የሌሎች ህመሞች ያልተመዘገቡ መድኃኒቶች፣ ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነታቸው የማይታወቅ፣ በኮንትሮባንድ የገቡና ሕጋዊ ደረሰኝ የሌላቸው መድኃኒቶች እንደሆኑ ተገልፅዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በሰጡት መግለጫ መስሪያ ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት በርካታ የቁጥጥር ተግባራትን እንዳከናወነ አስረድተዋል።
ተቋሙ የሕብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅ በምግብ፣ መድኃኒት፣ በህክምና መሳሪያዎች፣ በውበት መጠበቅያና በትምባሆ ዙሪያ ከክልሎች ጋር በመሆን ባካሄደው ቁጥጥር አበረታች ውጤት ማስመዝገቡ ተገልፅዋል።
ከምግብ ጋር በተያያዘ በአምራቾችና አስመጪዎችና አከፋፋዮች ላይ በአጠቃላይ 285 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 384 የፍቃድ ስረዛ፣ 39 የእሸጋና 310 የእገዳ እርምጃ ተወሰዷልም ነው ያሉት።
ከመድኃኒት ጋር በተያያዘም ግምታቸው ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ መድሃኒቶች በሕብረተሰብ ጤና ላይ ችግር ከማድረሳቸው በፊት ከክልሎች ጋር በመተባበር እንዲወገዱ መደረጉን ዋና ዳይሬክተሯ ሄራን ገርባ አስታውቀዋል።
በመሀመድ ራህመቶ